​አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድናቸውን ለቀው ወደ ሰበታ አምርተዋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘውን ሰበታ ከተማ የሚመሩት አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እና ረዳታቸው እንዲሁም የቴክኒክ ዳይሬክተሩ በአሁኑ ሰዓት ድሬዳዋ አይገኙም።

በዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች እስካሁን አንዱን ብቻ ያሸነፈው ሰበታ ከተማ እጅግ በከፋ የውጤት ማጣት ጉዞ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። በትናንትናው ዕለትም በአዲስ አዳጊው የመዲናው ክለብ አምስት ግቦችን አስተናግዶ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል። ይህ የውጤት ማጣት ያሳሰባቸው የሚመስሉት የክለቡ አመራሮችም የቡድኑን ዋና አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው፣ ምክትል አሠልጣኝ ታደሠ አዲስ እና ቴክኒካል ዳይሬክተር ፍቅሩ ተፈራን ለማነጋገር ጥሪ እንዳቀረቡላቸው አውቀናል።

ሦስቱ ግለሰቦችም ጥሪውን ተከትሎ በዛሬው ዕለት ድሬዳዋ የሚገኘው ስብስባቸውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ አድርገዋል። ነገ ረፋድ 4 ሰዓት ሰበታ የሚገኘው የክለቡ ጽሕፈት ቤትም ጥሪ ካቀረበላቸው የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴዎችን ጋር ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ዋና እና ረዳት አሠልጣኙ ከቡድኑ ጋር አለመገኘታቸውን ተከትሎ በሰበታ በምክትል አሠልጣኝነት ረዘም ላሉ ዓመታት ግልጋሎት የሰጡት ብርሃኑ ደበሌ እና ክረምት ላይ ስብስቡን የተቀላቀሉት ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም ከሦስት ሳምንታት በኋላ ዳግም ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ተደርጎ ስብስቡን ልምምድ እንዲያሰሩ ተደርጓል። አሠልጣኞቹም ዛሬ ወደ ድሬዳዋ እንዳቀኑ ሰምተናል።