​የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 0-0 ወልቂጤ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ያለ ጎል ከተጠናቀቀው የምሽቱ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው እና በመጀመሪያው እና በሁለተኛው አጋማሽ ስለታየው ሁለት አይነት እንቅስቃሴ…?

በመጀመሪያው አርባ አምስት ላይ የቡድናችን ኢንቴንሲቲ ከፍተኛ ነበር፡፡ግን አማካዮቻችን ቢጫ ካርድ በማየታቸው ከኳስ ውጪ ያላቸውን እንቅስቃሴ እንዲያወርዱ እና ኳሱን ሲያገኙ ብቻ እንዲጫወቱ አድርገናል፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ ኢንቴንሲቲ እግር ኳስ ነበር ስንጫወት የነበረው። የግድ አካላዊ ግንኙነት አለው፡፡ሁለተኛ ቢጫ ካዩ ቁጥራችን ሊጎል ነው፡፡ስለዚህ ኳሱ ሲደርሳቸው እንዲጫወቱ ከኳስ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ ላይ ብዙም ትኩረት እንዳያደርጉ ስለ መከርኳቸው ነው። ይህም ታክቲካል ነው፡፡

ይህ ፈጣን ማጥቃት የአንተ አጨዋወት ሆኖ በፕሪምየር ሊጉ ይቀጥላል?

የተጀመረ አጨዋወት ነው ያለቀለት አደለም። ምን አልባት ጥቂት ፐርሰንት ነው ይህንን አጨዋወት የሞከርነው። ገና እየሰራን ስንሄድ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ከፍተኛ ግለት ያለውን ኳስ እንደምንጫወት እርግጠኛ ነኝ።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

በመጀመሪያው አጋማሽ መበለጥ እና በሁለተኛው አጋማሽ ስለ መሻሻል…?

ሁለተኛው አርባ አምስት ደቂቃ በራሱ ለእኔ መሻሻል የሚባልም አደለም፡፡ ቡድናችን ዛሬ የሚገባውን ያህል ሰርቷል ማለት አይቻልም። እንቅስቃሴያችን በአጠቃላይ ጥሩ አደለንም በሚል ብንይዘው ጥሩ ነው፡፡ስለዚህ መስራት የሚገባን ነገር አለ። መስራት አለብን። ብዙ ተጫዋቾቻችን የነገርኳቸውን ስራ አደለም የሰሩት። በታክቲካል ዲሲፕሊን ራሱ ጥሩ የሚባል አደለም። ያው አቻ መውጣታችን አያንስም። ይበዛብን ይሆን እንጂ አያንስም፡፡

ሊጉ እየከበደ መምጣቱ ለዛሬው ውጤት ምክንያት ይሆን?

አዲስ አሰልጣኝ ስለመጣ ተነሳሽነት ነበራቸው። ይሄ ኖርማል ነው። በዛ ልክ ደግሞ እኛ እንዲነሳሱ ብዙ ነገር ብለናል። ግን የእኛ ተጫዋቾች ዛሬ ጥሩ የሚባሉ አደለም። አጠቃላይ ግን እየከበደ ነው የሚሄደው ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ጨዋታ ጠንካራ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

የቡድኑ ደካማ ጎን…?

ዛሬ አማካዩ ነው። በጣም ደካማ የሚባል ነው። አማካዮቻችን የምንላቸውን እና ያልናቸውን ተግባራዊ አለማድጋቸው ነው። ሌላ ጊዜ አማካይ መስመራችን ጥሩ ነው ትጋቱም ከፍተኛ ነው። ዛሬ ግን ጥሩ አልነበርንም፡፡