​ሪፖርት | የሀብታሙ ጎል ሲዳማ ቡናን ሦስት ነጥብ አስገኝቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ሲዳማ ቡና በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠረው አንድ ጎል አዲስ አበባ ከተማን በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል።

ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይተው ለዛሬው ፍልሚያ የተዘጋጁት ሲዳማ ቡናዎች ሁለት ነጥብ ከጣሉበት ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በለውጦቹም ግርማ በቀለ እና ብሩክ ሙሉጌታ የጊት ጋትኩት እና ቴዎድሮስ በቀለን ቦታ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተቃራኒው ባሳለፍነው ሳምንት ሰበታ ከተማ ላይ አምስት ግቦችን አዝንበው ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የታረቁት አዲስ አበባ ከተማዎች አሸናፊ ቡድን አይቀየርም የሚለውን መርህ የተከተሉ በሚመስል መልኩ ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ቀርበዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ብድኖች ጨዋታ በ10ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህም ገና በጨዋታው ጅማሮ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የወጣው የመሐሪ መናን መስመር በመጠቀም እንዳለ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ሲዳማዎች መሐሪ በጉዳት ሲወጣ በቶሎ በቦታው ቅያሪ ሳያደርጉ ሦስት ደቂቃዎች የተቆጠሩ ሲሆን አዲስ አበባዎችም ይህንን የሰው ብልጫ ለመጠቀም ከደቂቃ በኋላ ሌላ ጥቃት በተመሳሳይ መስመር ለመሰንዘር ሞክረው ነበር። የጨዋታውን ሂደት በራሳቸው መንገድ እየቃኙ የሚገኙት የአሠልጣኝ ደምሰው ተጫዋቾች በሩብ ሰዓት በአማካያቸው ሙሉቀን አዲሱ የርቀት ኳስ ሌላ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል።

አጀማመራቸው ብዙም ጥሩ ያልሆነው ሲዳማች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ አንፃራዊ ብልጫ ቢኖራቸውም በተለይ በቀኝ መስመር ከፍተኛ ጫና በዝቶባቸው ታይቷል። በ25ኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው ተስፋዬ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተገኘውን የቅጣት ምት ሮቤል ግርማ በአስገራሚ ሁኔታ ከቀኝ መስመር ማሻማት በሚመስል መልኩ ልኮት ኳስ የግቡን አግዳሚ ነክታ ወደ ውጪ ወጣች እንጂ ሊመሩ ይችሉ ነበር። ቡድኑ ግን በ33ኛው ደቂቃ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ አበባን የግብ ዘብ ዳንኤል ተሾመ በቆመ ኳስ ፈትኗል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በክፍት ጨዋታ ለጎል የቀረበ ጥቃት ፈፅመዋል። በዚህም አዲስ አበባዎች ለማጥቃት ግብ ክልላቸውን ለቀው ሲወጡ የተረከቡትን ኳስ በፈጣን ሽግግር ወደሳጥን ወስደውት ፍሬው ጥሩ ኳስ ወደግብ ልኳል። ነገርግን ተጫዋቹ የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ሳሙኤል አስፈሪ በቅብብል ወቅት የሰራውን ስህተት ተከትሎ ሀብታሙ ያገኘውን ኳስ ለይገዙ ሰጥቶት ይገዙ እጅግ ጥብቅ ኳስ ወደግብ ቢመታም ግብ ጠባቂው ዳንኤል በሚገርም ቅልጥፍና ራሱን ለጉዳት አጋልጦ አምክኖታል።

አንድ አንድ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግ በተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ሲታትሩ ታይቷል። በአንፃሩ የተሻለ የነበረው ሲዳማ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የነበረውን ድክመት በማስተካከል ነቃ ያለ ጅማሮ አድርጎ በ59ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። በዚህም በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ራሱን ነፃ አድርጎ የቆመው ሀብታሙ ገዛኸኝ ከይገዙ ቦጋለ የደረሰውን ኳስ በመጠቀም የዳንኤልን መረብ ደፍሯል።

ወደ መሪነት የተሸጋገሩት ሲዳማዎች በ65ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ ሊያገኙ ነበር። የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ይገዙ (ከኦሮ-አጎሮ) በተጠቀሰው ደቂቃ ከዳዊት ጥሩ ተጫዋች ሰንጣቂ ኳስ ደርሶት ሞክሮት ነበር። አዲስ አበባ ከተማዎች ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተጫዋች ለውጥ ቢያደርጉም እምብዛም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርቷል። ሲዳማ ደግሞ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት ኳሱን በመቆጣጠር ጨዋታውን ይዞ ማውጣት ምርጫው አድርጎ ተንቀሳቅሷል። በ82ኛው ደቂቃ ግን ፈጣን ኳስ የደረሰው ይገዙ በውድድሩ ያስቆጠረውን ጎሎች ብዛት 9 ለማድረስ ቢሞክርም የግብ ዘቡ ዳንኤል በዘጠነኛው ጎል እና ይገዙ መሐል በመቆም ዕድሉን አክሽፎታል። ጭማሪ ደቂቃ ሊታይ ሲል ደግሞ ፍሬው በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የመጨረሻ ሙከራ አድርጎ ተመልሷል። ዳኛው ፊሽካቸው በሚጠበቅበት ሰዓት ደግሞ ኦዶንጎ ቡድኑን አቻ ማረጊያ ወርቃማ ዕድል አግኝቶ አምክኗል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።

ጨዋታውን 1ለ0 ያሸነፈው ሲዳማ ቡና ነጥቡን 22 በማድረስ ከነበረበት 7ኛ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሦስት ነጥብ ያስረከበው አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከሰበሰበው ነጥብ እኩል 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።