በፈረንሳይ እና በቤልጂየም ሊግ ክለቦች የሚጫወቱት ያሲን ቤንዚያ እና ሶፊያን ሃኒ በአሠልጣኝ ክርስቲያን ጎርኩፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን ዛሬ በብሊዳ ከተማ የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን በሚገጥምበት ጨዋታም ተሰልፈው ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሴንት አውቢን በተሰኘች የፈረንሳይ መንደር ውስጥ የተወለደውና የሊዮን አካዳሚ ውጤት የሆነው ያሲን ቤንዚያ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ሲሆን በፈረንሳይ ሊግ 1 ለሚሳተፈው ሊል እየተጫወተ ይገኛል። በፈረንሳይ ከ16 ዓመት ብሔራዊ ቡድን ጀምሮ በየዕድሜ ደረጃው ባሉ ቡድኖች ተጫውቶ ያሳለፈውና በአንድ ወቅትም ‘አዲሱ ካሪም ቤንዜማ’ የሚል ቅፅል ስም አግኝቶ የነበረው ቤንዚያ ከአልጄሪያው የእግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት መሃመድ ራውራዋ ጋር ካደረገው ውይይት በኋላ የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድንን ማሊያ ለብሶ ለመጫወት ወስኗል። ተጫዋቹ ለአልጄሪያ መጫወት ሁልጊዜ በልቡ የነበረ ፍላጎት እንደሆነና ከቤተሰቡ ጋርም ተወያይቶ ለወላጆቹ ሃገር መጫወት እንደወሰነ ተናግሯል።
በተመሳሳይ አይቭሪ ሱር ሲዬን በምትባል በፓሪስ አቅራቢያ በምትገኝ ትንሽ ከተማ የተወለደውና ለቤልጂየሙ ሜቼለን ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘው ሶፊያን ሃኒ ለመጀመሪያ ጊዜ የብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ደርሶታል። ለፈረንሳይ ወጣት ቡድኖች ተጫውቶ ያሳለፈው የአጥቂ አማካይ ከ5 ዓመታት በፊት ለአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ያለውን ፍላጎት ያሳወቀ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በቡድኑ ውስጥ አልተካተተም ነበር። የቤልጂየም ሊግ የኮከብ ግብ አግቢዎችን ሰንጠረዥ በ14 ግቦች እየመራ የሚገኘው ሃኒ በውድድር ዓመቱ ያሳየው ብቃት ለብሔራዊ ቡድኑ ለመጠራት በቂ እንደሆነ የሚከራከሩ ብዙዎች ቢሆኑም አሁን በቡድኑ ውስጥ መካተት የቻለው የዳይናሞ ዛግሬቡ አጥቂ ሂላል ሱዳኒ በመጨረሻ ሰዐት በመጎዳቱ ነው።
የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን ዛሬ ከምሽቱ 4፡30 ላይ ቢልዳ በሚገኘው ሙስታፋ ቻከር ስታዲየም የሚያስተናግድ ይሆናል።