የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ 17ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ የ17ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች መሪው መድን ሲሸነፍ ነቀምት ወደ ፉክክሩ የተመለሰበትን ወሳኝ ድል አስመዝግቧል፡፡ ደቡብ ፖሊስ እና ፌዴራል ፖሊስ በበኩላቸው ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ኢትዮጵያ መድን ተሸንፏል

ተጠባቂው የመዲናይቱ ክለቦች ጨዋታ ረፋድ 3፡00 ሰዓት ሲል ተጀምሯል፡፡ በመርሐ-ግብሩ ኢትዮጵያ መድን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ የካ ክፍለ ከተማ በበኩሉ ወደ አንደኛው ሊግ ላለመውረድ ያደረጉት ትንቅንቅ ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝነት ያለው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን መመልከት ብንችልም ከግብ ለመገናኘት ተደጋጋሚ ጥቃትን በመሰንዘሩ ረገድ መድኖች ሻል ብለው ታይተዋል፡፡ 7ኛው ደቂቃ ላይም እዮብ ገብረማርያም እጅግ አስቆጪ አጋጣሚን አግኝቶ ባልተጠቀመባት ሙከራ ቀዳሚዎች ሆነዋል፡፡ በአንፃሩ የካዎች የግብ ሙከራ ብልጫ ቢወሰድባቸውም የመድን ተከላካዮች የሚሰሯቸውን ስህተቶች ከመጠቀም ወደኋላ አላሉም። በዚህም 20ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሱን በቀለ ከቀኝ የመድን የግብ ክልል የፈጠረውን ዕድል አላዛር ዝናቡ ተጠቅሞ ወደ ጎልነት በመለወጥ የካን መሪ አድርጓል፡፡ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ይበልጥ በአንድ ሁለት ቅብብል እና በተሻጋሪ ኳሶች አቻ ለመሆን ሲታትሩ የነበሩት የአሰልጣኝ በፀሎት ተጫዋቾች እጅግ ያለቀላቸውን ዕድሎች አግኝተው በማይታመን መልኩ ሲያመክኑ ውለዋል፡፡ በተለይ ኪቲካ ጀማ 28ኛ ደቂቃ ላይ ለማሻማት የሞከራት ኳስ የየካው ግብ ጠባቂ ሚሊዮን ሰለሞን ተዘናግቶ ወደ ጎልነት ለመለወጥ ከጫፍ ብትደርስም በተከላካዮች ርብርብ ልትወጣ ችላለች፡፡

በሌላ ሙከራ ያሬድ ዳርዛ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ የሰጠውን እና እዮብ ገብረማርያም ከግብ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት እንዲሁም ቢኒያም ካሳሁን ከማዕዘን አሻምቶ ያሬድ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት ሙከራ የመድኖች የበላይነት ያሳዩ ዕድሎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ከግራ አቅጣጫ አማካዩ ቢኒያም ካሳሁን ከኪቲካ ጀማ ጋር ባደረገው ቅብብል የተገኘችን መልካም ዕድል ያሬድ ዳርዛ ወደ ጎልነት በመለወጥ መድንን 1ለ1 አድርጓል፡፡

ፍፁም የመድን የበላይነት በተንፀባረቀበት እና የካ ክፍለ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የአጨዋወት መንገድ የመድንን ደካማ የመከላከል አወቃቀር ለመጠቀም በታተሩበት ሁለተኛው አጋማሽ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ብንመለከትም ሥል ያልነበረው የመድን የአጥቂ ክፍል በቀላሉ ሲያመክኗቸው ውለዋል፡፡ 51ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ከቅጣት ምት ሲያሻማ ኪቲካ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ያወጣበት እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኪቲካ ከግራ በኩል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ የላካት ኳስ እዮብ ገብረማርያም መረጋጋት ተስኖት መጠቀም ያልቻላት አጋጣሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ጨዋታው 60ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በመከላከሉ ከወትሮው መሳሳት ይታይባቸው የነበሩት መድኖች በየካ የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ ግብ አስተናግደዋል፡፡ ከቀኝ በኩል ኤፍሱን በቀለ ያሳለፈለትን ኳስ በመጠቀም አላዛር ዝናቡ ወደ ሳጥን እየነዳ ገብቶ እጅግ ግሩም ጎል በጆርጅ ደስታ መረብ ላይ አሳርፎ የካን ወደ 2ለ1 አሸጋግሯል፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በርካታ ዕድሎችን መድኖች ቢያገኝም ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ሊጠቀሙ አልቻሉም፡፡በተለይ አጥቂው ያሬድ ዳርዛ አራት ወደ ጎልነት ሊቀየሩ የሚችሉ ዕድሎችን አግኝቶ ይታይበት በነበረው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ሲያመክን ታይቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ አብዱለጢፍ ሙራድ ከመስመር እና ከቅጣት የተገኙትን ኳሶች በግንባር ገጭቶ ሁለት ጊዜ ብረት የመለሰበት አጋጣሚዎች በመጨረሻ ደቂቃ መድንን ለአሸናፊነት ሊያበቁ የተቃረቡ ቢመስሉም ጨዋታው በየካ 2ለ1 ድል ተጠናቋል፡፡

ነቀምት ከተማ ወደ ፉክክሩ መመለሱን ያረጋገጠበትን ድል አስመዝግቧል

8፡00 ሰዓት ላይ በጉለሌ እና ነቀምት ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ተጀምሯል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የነቀምቶች የበላይነት በደንብ ተፅኖ ፈጥሮ የታየበት ነበር። በተለይ ረጃጅም ኳሶቻቸውን ለፊት አጥቂዎቻቸው በመጣል ጎል ለማስቆጠር ጥረት ማድረግ የጀመሩት ገና ከጅመሩ ነበር፡፡ በአንፃሩ ጉለሌዎች ኳስን በመያዝ በቅብብሎሽ ለመጫወት ቢጥሩም ሙሉ በሙሉ በሚቻል ሁኔታ በነቀምት ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ እንደገለፅነው ነቀምቶች መሀል ሜዳ ላይ በዘሪሁን ይልማ እና ዋቁማ ዲንሳ የሚነሱትን ኳሶች ወደ መስመር በማሳለፍ በረጅሙ ለአጥቂዎቹ ኢብሳ በፍቃዱ ፣ ዳንኤል ዳዊት እና ቦና ቦካ በመላክ ጎሎችን ለማግኘት ታትረዋል፡፡

14ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ሰምሮ ግብ ጠባቂው ሌሊሳ ታዬ ከቅጣት ምት ያሻማትን ኳስ በተደጋጋሚ በግንባር በመግጨት በየጨዋታዎቹ ልዩነት ፈጣሪ ሲሆን የምንመለከተው ኢብሳ በፍቃዱ አመቻችቶ ሲያቀብለው ቦና ቦካ በግንባር ከመረብ በማሰረፍ ነቅምት መሪ ሆኗል፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ኳሶችን ወደ መስመር በማውጣት የረጃጅም ኳስ አጠቃቀማቸውን ያጎለበቱት የአሰልጣኝ ተካልኝ ዳርጌ ተጫዋቾች በኢብሳ ፣ ቦና እና ዳንኤል ተጨማሪ ጎል ለማከል ፋታ የለሽ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡ 38ኛው ደቂቃ ላይ ከምኞት ማርቆስ የተነሳች ኳስ ኢብሳ ጋር ደርሳ ተጫዋቹ በቀጥታ ወደ ጎል ሲመታ ግብ ጠባቂው ፓላክ ቾል ሲተፋው አጠገቡ የነበረው ዳንኤል ዳዊት ወደ ጎልነት ለውጧት የነቀምት መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ብሏል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲቀጥል ከመጀመሪያው አጋማሽ በሙከራም ሆነ በእንቅስቃሴ እጅግ ቀዝቃዞ የታየበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 2ለ0 እየተመሩ አጋማሹን የቀጠሉት ጉለሌዎች ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት በተለይ በአንድ ሁለት የኳስ ንክኪ ልዩነት ለመፍጠር በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም የጠሩ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ረገድ ግን እጅጉን ደካሞች ሆነው ታይተዋል፡፡ በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶች መለያቸው የሆኑት ነቀምቶች በኢብሳ በፍቃዱ እና ምኞት ማርቆስ አማካኝነት ተጨማሪ ግብን ለማከል በተደጋጋሚ ሲጥሩ ቢስተዋልም ወደ ጎልነት መለወጥ ግን አልቻሉም፡፡ 84ኛ ደቂቃ ላይ በሽግግር ሂደት ዳንኤል ዳዊት ያገኛትን ኳስ በቀጥታ መትቶ ግብ ጠባቂው ፓላክ ቾል ከመለሰበት ሙከራ ውጪ ከመጀመሪያው አርባ አምስት የተቀዛቀዘው አጋማሽ ተመልክተን 2ለ0 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

የሁለቱ የፖሊስ ክለቦች ጨዋታ አሰልቺ ሆኖ ያለ ግብ ተጠናቋል

10፡00 ሰዓት ሲል በሁለት የፖሊስ ክለቦች መካከል የተደረገው ጨዋታ ጀምሯል፡፡ ደቡብ ፖሊስ እና ፌዴራል ፖሊስን ያገናኘው ጨዋታ እጅጉን አሰልቺ እና ለእይታ ሳቢ ያልነበረ ሆኖ አልፏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የፌዴራል ፖሊሱ ተመስገን ታሪኩ ለማሻማት ሲል የግቡ አግዳሚ ብረት ነክቶ የወጣበት እና 40ኛው ደቂቃ ላይ እሱባለው ፍቅሬ ከማዕዘን አሻምቶ ታምራት እያሱ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው ታሪኩ አርዳ ከያዘበት ኳስ ውጪ ተጨማሪ አጋጣሚን መመልከት ሳንችል በአሰልቺነቱ ጨዋታው 0ለ0 ተጠናቋል፡፡