‹‹ በዛሬው ጨዋታ የተሻለው ቡድን ያሸንፋል›› የአልጄርያ አሰልጣኝ አዚድ ቺህ

የአልጄርያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ትላንት ለዛሬው የመልስ ጨዋታ ቡድናቸውን በአዲስ አበባ ስታድየም ልምምድ ካሰሩ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ ጨዋታ እንዲሁም ስለመልሱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እጅግ በጣም ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ቡድኑን በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ጨምሮ በተለያየ ጊዜ የተመልከትኩት ቡድን በመሆኑ በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ የአልጀርሱ ጨዋታ በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም በጣም ጥሩ ተጋጣሚ ነበር፡፡ የመጀመርያውን ጨዋታ አሸንፈን በመምጣታችን አድቫንቴጃችንን ማስጠበቅ እንፈልጋለን፡፡ ›› ሲሉ የተናገሩት አዚድ በጨዋታው ጥሩ የሚንቀሳቀሰው ቡድን አሸናፊ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በጨዋታው ስለሚሆነው ነገር መናገር አልችልም፡፡ አልጀርስ ላይ 1-0 አሸንፈናል፡፡ አሁን ደግሞ የመልስ ጨዋታ ልንጫወት ነው፡፡ ውጤቱ ለሁለታችንም ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ ጨዋታውን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጠኝነት ጨዋታው ለሁለቱም ቡድን ቀላል አይሆንም፡፡ ያው የተሻለው ቡድን ያሸንፋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን የበለጠ ከተጫወተ ያሸንፍ እኛም ጥሩ ቀን ካሳለፍን እናሸንፍ››

የአልጄርያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የወንዶች ብሄራዊ ቡድን ሞዴልን በመከተል በርካታ የአልጄርያ የዘር ግንድ ያላቸው ፈረንሳውያንን የቡድኑ አባል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የአልጄርያ መንገድ በርካታ አስተያየቶችን ቢያስተናግድም አሰልጣኝ አዚድ ግን ማንኛውም አልጄርያዊ የብሄራዊ ቡድኑን ማልያ የመልበስ መብት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ ወደ አዲስ አበባ ይዘናቸው የመጣናቸው ተጫዋቾች በሙሉ በብሄራዊ ቡድን የነበሩ ልጆች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ አውሮፓ ይጫወቱ እንጂ አልጄርያውያን ናቸው፡፡ ስለዚህ የሃገራቸውን ማልያ የመልበስ መብት አላቸው፡፡ እነሱን መጥራት ከውጤት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡››

አሰልጣኙ በመጨረሻም ኢትዮጵያ እና አልጄርያ በሁለቱም ፆታዎች ላይ በተመሳሳይ ወቅት ስለመገናኘታቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ትኩረታቸው ሴቶች እግርኳስ ላይ እንደሆነ የሚያሳይ አስተያየትም ሰጥተዋል፡፡

‹‹ አጋጣሚው በጣም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በእግርኳስ እዲህ አይነት መገጣጠም ሁሌም ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ማውራት ያለብን ስለሴቶቹ ብቻ ነው፡፡ የወንድ እና የሴት እግርኳስ የተለያየ ነው፡፡ የሴቶች እግርኳስ ላይ ብዙ ነገር መሰራት አለበት፡፡ የሴቶችን እግርኳስ ብዙ ማበረታታት አለባችሁ፡፡ ሴቶች እግርኳስ ላይ ብዙ መሻሻል ያለበት ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ውድድር ማዘጋጀት ላይ ማለቴ ብቻ አይደለም፡፡ ሴቶች በተለያዩ መስኮች ብዙ ነገር ሲያደርጉ እያየን ነው፡፡›› ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

የአልጄርያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ጨዋታው በሚደረግበት አዲስ አበባ ስታድየም ትላንት ልምምዱን የሰራ ሲሆን የሜዳው ስፋት ለመጠቀም ፣ በጫና ውስጥ ሆኖ መቀባበልን እና አንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ አሸናፊ መሆንን ያለሙ ልምምዶችን ሰርቷል፡፡ የአየር ላይ ኳስ እና የቆመ ኳስ አጠቃቀምም የልምምዳቸው አካል ነበር፡፡

የሁለቱ ቡድነች ጨዋታ ዛሬ በ10፡00 በአዲስ አበባ ስታድየም ሲደረግ በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ቡድን በቀጣዩ የማጣርያ ዙር ኬንያ ይገጥማል፡፡

IMG_5975 IMG_5959

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *