ጋቦን 2017፡ መሃመድ ሳላ ግብፅን ታድጓል 

በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ካዱና ላይ የተገናኙት ናይጄሪያ እና ግብፅ 1-1 ተለያይተዋል፡፡ አልጄሪያ ኢትዮጵያ ላይ የግብ ናዳ ስታወርድ ማሊ የምድብ መሪነቷን ያጠናከረችበትን ድል አስመዝግባለች፡፡

የምድብ ሰባት መሪዋ ግብፅ ወሳኝ የሆነ አንድ ነጥብ ከናይጄሪያ ላይ በመውሰድ ከምድብ የማለፍ ተስፋዋን አለምልማለች፡፡ በአማዱ ቤሌ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ስፑር ኢግሎቹ ኢቴቦ ኦግሄንካሮ ግብ ቢመሩም መሃመድ ሳላ የሁለተኛው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በባከነ ሰዓት ያስቆጠራት ግብ ጨዋታውን በአቻ ውጤት እንዲያልቅ አድርጓል፡፡ ካዱና የሚገኘው ስታዲየሚ ተመልካች የመያዝ አቅሙ 25000 ቢሆንም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ደጋፊ ጨዋታውን ተመልክቷል፡፡ ምድቡን ግብፅ በሰባት ነጥብ ስትመራ ናይጄሪያ በአምስት ትከተላለች፡፡

በምድብ አንድ ቱኒዚያ ቶጎን 1-0 አሸንፋለች፡፡ የቱኒዚያን የድል ግብ ያሰመዘገበው የቀድሞ የኤስፔራንስ የአጥቂ አማካይ የሱፍ ሳክኒ ነው፡፡ ድሉን ተከትሎ ቱኒዚያ ቶጎን እና ላይቤሪያን በግብ ክፍያ በመብለጥ በስድስት ነጥብ አንደኛ ሆናለች፡፡

ናውኩቾ ላይ ባለሜዳዋ ሞሪታንያ ጋምቢያን 2-1 ማሸነፍ ችላለች፡፡ ሼክ ሞላይ ካሊል የሞሪታንያን ሁለት ግቦች ሲያስቆጥር ሙስጠፋ ካራዮል ጋምቢያን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ በስሙ አስመዝግቧል፡፡ ሞሪታንያ ነጥቧን ወደ ስድስት በማሳደግ ከካሜሮን ጋር ምድብ 13ን መምራት ጀምራለች፡፡

በምድብ 12 ከሶስት ጨዋታዎች በኃላም ሁሉም ሃገራት የማለፍ ተስፋቸው ሳይማጠጥ የመልስ ጨዋታዎቻቸውን መጠበቅ ጀምረዋል፡፡ ኮናክሬ ላይ ጊኒ ከማላዊ ካለግብ ጨዋታቸውን ሲፈፅሙ የምድቡ መሪ ስዋዝላንድ ከዚምባቡዌ 1-1 ተለያይተዋል፡፡ ፊሊክ ባደንሆርስት ስዋዚላንድን ቀዳሚ ሲያደርግ ስዋዚላንዱ ንዶኩኢቶ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል፡፡ ስዋዚላንድ እና ዚምባቡዌ ምድብ በአምስት ነጥብ ሲመሩ ማላዊ እና ጊኒ ሁለት ነጥብ በመያዝ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

የ2015 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ኮትዲቯር አቢጃን ላይ ሱዳንን በጀርቪሆ ግብ 1-0 ስትረታ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅዋ ጋቦን ሴራሊዮንን 2-1 ፋራንስቪል ላይ መርታት ችላለች፡፡ የጋቦንን ግቦች ፒየር ኤምሪክ ኦባምያንግ በፍፁም ቅጣት ምት እና የአል አሃሊው አጥቂ ማሊክ ኢቮና አስቆጥረዋል፡፡ ሼካ የሴራሊዮንን ብቸኛ ግብ በስሙ አስመዝግቧል፡፡ ምድብ ዘጠኝን ጋቦን በሰባት ስትመራ ኮትቯር በስድስት ትከተላለች፡፡

ማሊ በሞላ ዋጉ የ80ኛ ደቂቃ ግብ ታግዛ ኤኳቶሪያል ጊኒን አሸንፋለች፡፡ ምድብ ሶስትን ማሊ በሰባት ነጥብ ስትመራ ቤኒን በአምስት ትከተላለች፡፡

ኢትዮጵያ የምትገኘበትን ምድብን አልጄሪያ በዘጠኝ ነጥብ ስትመራ የግብ ናዳ የወረደባት ኢትዮጵያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ነች፡፡

PicsArt_1458976665258

የአርብ ውጤቶች

አልጄሪያ 7-1 ኢትዮጵያ

ናይጄሪያ 1-1 ግብፅ

ማሊ 1-0 ኤኳቶሪያል ጊኒ

ስዋዚላንድ 1-1 ዚምባቡዌ

ጊኒ 0-0 ማላዊ

ሞሪታንያ 2-1 ጋምቢያ

ቱኒዚያ 1-0 ቶጎ

ኮትዲቯር 1-0 ሱዳን

ጋቦን 2-1 ሴራሊዮን

gabonfoot

የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ዛሬም ቀጥሎ ሲውል በምድብ 13 ካሜሮን ከደቡብ አፍሪካ፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ ከአንጎላ፣ ቡርኪናፋሶ ከዩጋንዳ እንዲሁም ኬፕ ቬርዴ ከሞሮኮ የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ግምትን አግኝቷል፡፡ የካሜሮን እና ደቡብ አፍሪካ ጨዋታን ባምላክ ተሰማ በመሃል ዳኝነት ይመራል፡፡

በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ሲሸልስ እና ሌሌቶም ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

የዛሬ ጨዋታዎች

15፡00 – ብሩንዲ ከ ናሚቢያ (ፕሪንስ ሊዊ ራዋጋሶር)

15፡00 – ሞሪሺየስ ከ ሩዋንዳ (ቤል ቩ)

15፡30 – ካሜሮን ከ ደቡብ አፍሪካ (ሊምብ ኦምኒስፖርትስ ስታዲየም)

15፡30 – ዲ.ሪ. ኮንጎ ከ አንጎላ (ስታደ ደስ ማርትየርስ)

16፡00 – ኬፕ ቬርዴ ከ ሞሮኮ (ፕሪያ)

16፡30 – ሲሸልስ ከ ሌሌቶ (ዩኒቲ ስታዲየም)

18፡30 ቡርኪና ፋሶ ከ ዩጋንዳ (4 ኦዉት)

19፡00 – ሴኔጋል ከ ኒጀር (ስታደ ሊዮፖልድ ሴዳር ሰንጋሆር)

12721748_796707187127118_478623347_n-1

ፎቶዎች – አፍሪካ ቶፕ ስፖርት እና ጎል.ኮም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *