ኢትዮጵያ በአልጄርያ በድምር ውጤት 2-1 ተሸንፋ ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ተሰናበተች

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከአልጄርያ ጋር ባደረገው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት በመለያየት ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር መሰናበቱን አረጋግጧል፡፡

ሉሲዎቹ አልጀርስ ላይባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታ የ1-0 ሽንፈት አስተናግደው በመመለሳቸው በግቦች ልዩነት ማሸነፍን ብቻ አላማ አድርገው ቢገቡም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች በተቆጠረባቸው ግብ አቻ ተለያይተው በ2-1 ድምር ውጤት ከውድድሩ ተሰናብተዋል፡፡

ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ሉሲዎቹ ሲሆኑ በ33ኛው ደቂቃ ከቅታት ምት የተሸገረውን ኳስ ተጠቅማ ሎዛ አበራ ግብ አስቆጥራለች፡፡ ሎዛ ያስቆጠረችው ግብ ሉሲዎቹ በ4 አመት ውስጥ ያስቆጠሩት የመጀመርያ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ ሉሲዎቹ በተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጨማሪ ግቦች ያስቆጥራሉ ተብሎ ሲጠበቅ በተቃራኒው ረጃጅም ኳሶች እና አላማ የሌላቸው ቅብብሎች በማድረግ ጨዋታው ወደ መገባደጃው እስኪደርስ ድረስ የረባ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል፡፡

በ86ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ደሊላ ዜሮኪ ኳሱን ለማውጣት ከግቧ የወጣችው ዳግማዊትን ቀድማ በግንባሯ በመግጨት የአልጄርያን ወሳኝ ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡ በአልጀርሱ ጨዋታ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈችው ዜሮኪ አዲስ አበባ ላይም የአቻነቷን ግብ በማስቆጠር አልጄርያ ወደ ተከታዩ ዙር እንድታልፍ ትልቁን ድርሻ ተወጥታለች፡፡

አሸናፊዋ አልጄርያ በቀጣዩ የማጣርያ ዙር ኬንን የምትገጥም ሲሆን ተሸናፊዋ ኢትዮጵያ ለተከታታይ 3ኛ ጊዜ ለአፍሪካ ሴቶች ዋነጫ ማለፍ ሳትችል ቀርታለች፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *