“አሁንም የማለፍ ተስፋችን አልተሟጠጠም” አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

ኢትዮጵያ በምድቡ 3ኛ ጨዋታ ብሊዳ ላይ አስደንጋጭ 7-1 ሽንፈት ማስተናገዷን ተከትሎ ወደ ጋቦን የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋዋ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡

ከሽንፈቱ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ አፍቃርያን በቡድናቸው ተስፋ እንደቆረጡ በተለያዩ መንገዶች ቢገልፁም አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለአፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ተስፋቸው ገና እንዳላበቃ ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል፡፡

” የ7-1 ሽንፈት ቢደርስብንም ያጣነው 3 ነጥብ ብቻ ነው፡፡ የማለፍ ተስፋችንም ገና አልተሟጠጠም፡፡ በተለይም የማክሰኞውን ጨዋታ በማሸነፍ የማለፍ ተስፋችን ላይ ህይወት የመዝራት እድሉ አለን፡፡ ”

የምድቡን 4ኛ ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጉት ዋልያዎቹ በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ የህዝቡ ድጋፍ እንደሚኖራቸውም ተስፋ አድርገዋል፡፡

“አልጄርያ የሜዳ አድቫንቴጅ እና የህዝባቸው ድጋፍ ለውጤታቸው እገዛ አድርጎላቸዋል፡፡ ይህ እገዛ ደግሞ ማክሰኞ በሚደረገው ጨዋታ እኛ ላይ እንደሚኖር ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡

“በአጠቃላይ ውጤቱ ሞራላችን ላይ ከልክ በላይ ተፅእኖ አይፈጥርብንም፡፡ ምክንያቱም በምድባችን ያጋጠመን የመጀመርያ ሽንፈት ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ላይም እንገኛለን፡፡ ”

ምንጭ – ዲዚ ፉት ፣ ኤል ሞጃሂድ

ፎቶ – በዲዚ ፉት

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *