ብሄራዊ ቡድናችን ከነገው ጨዋታ በፊት ልምምዱን ዛሬ አድርጓል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአልጀርስ በግብጽ አድርጎ ትላንት አዲስ አበባ ከገባ በኋላ እረፍት በማድረግ ዛሬ ጠዋት ልምምዱን ሰርቷል፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ በዛሬው ልምምዱ ቀለል ያሉ የማላቀቅያ ልምምዶች የሰሩ ሲሆን ቋሚ ተሰላፊዎቹን በሚለይ መልኩ ለሁለት በመከፈል ጨዋታ አድርገዋል፡፡ በ7-1 ሽንፈቱ ላይ ከነበረው አሰላለፍ ለውጦች የሚጠበቁ ሲሆን በተለይም አቤል ወይም ለአለም በዛሬው የልምምድ ጨዋታ ላይ ያልተሳተፈው ታሪክ ጌትነትን ተክተው በጨዋታው ይሰለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዋልያዎቹ ልምምድ ላይ የተስተዋለው መጠነኛ ግጭት ሌላው በስራው የተገኘውን ተመልካች ትኩረት የሳበ ክስተት ነበር፡፡ አማካዩ ጋቶች ፓኖም በልምምድ መሃል ጌታነህ ላይ ፋውል ሲሰራ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ደግሞ ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ ላይም ተመሳሳይ ፋውል ሰርቷል፡፡ በመቀጠል ደግሞ ሱሌይማን መሃመድ ላይ ከባድ ፋውል የፈፀመ ሲሆን ይህም ጌታነህ እና አንተነህ ጋቶችን ከሃይል አጨዋወቱ እንዲታቀብ እንዲነግሩት አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ በተነሳ ቅራኔም ተጫዋቾቹ ቃላት ሲለዋወጡ ተስተውሏል፡፡ የቡድኑ አምበል አስራት መገርሳ የተጫዋቾቹን አለመግባባት ለመፍታት ተጫዋቾችን በመሰብሰብ ረጅም ደቂቃዎች የፈጀ ንግግር ሲያደርጉም ታይተዋል፡፡

በቀዘቀዘና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ነገ አልጄርያን ሲያስተናግድ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ያለውን ተስፋ ለማለምለም የግድ በማሸነፍ ላይ ተመስርቶ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ በአንጻሩ አልጄርያ ጨዋታውን ካሸነፈች የጋቦን 2017 ትኬት መቁረጧን ከ90 በመቶ በላይ ታረጋግጣለች፡፡

PicsArt_1459157314213 PicsArt_1459157255032 PicsArt_1459157223326

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *