የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ባለፈው አርብ ኢትዮጵያ በአልጄርያ የ7-1 ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ ከሃላፊነታቸው እንዲለቁ ግፊት በርትቶባቸዋል፡፡ በተለይም የነገውን ጨዋታ ተከትሎ ራሳቸውን ከሃላፊነት እንደሚያነሱ ለሶከር ኢትዮጵያ የደረሳት መረጃ ያመለክታል፡፡
አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከፌዴሬሽኑ ጋር ያላቸው ልዩነት እየሰፋ ሲሆን ለፌዴሬሽኑ ሃላፊዎች በቅርቡ ራሳቸውን ከሃላፊነት እንደሚያነሱ ምልክቶች ማሳየታቸው ታውቋል፡፡ ከፌዴሬሽኑ አካባቢ ባገኘነው መረጃ ወደ አልጄርያ ከመጓዛቸው በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከፌዴሬሽኑ በቂ ድጋፍ እንደማይደረግላቸውና የአስተዳደር ስራዎችን ጭምር ለመስራት መገደዳቸውን መናገራቸው ፌዴሬሽኑን አላስደሰተም፡፡ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ እያደረገላቸው አላደረገልኝም በማለታቸው ምክንያት ከፌዴሬሽኑ ጋር ቅራኔ ውስጥ በመግባታቸው ፣ በውጤቱ መጥፋት እና በህዝቡ ጫና ምክንያት አሰልጣኙ ከሃላፊነታቸው በቅርቡ መልቀቃቸው እንደማይቀር ለፌዴሬሽኑ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌም ከፌዴሬሽኑ ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት በቀሪዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ቡድናቸውን የመምራት ፍላጎት እንደሌላቸውና ከአሰልጣኝነት ሹመታቸው ጀምሮ ከሁሉም አቅጣጫ ድጋፍ መነፈጋቸው ራሳቸውን ከሃላፊነት እንዲያገሉ እንዳቃረባቸው ተነግሯል፡፡
አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ባለፈው አመት ወደ ዋልያዎቹ አሰልጣኝነት መንበር መምጣታቸውን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ብሄራዊ ቡድን ውጤት ማስመዝገብ ከተሳነው ራሳቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ራሳቸውን ከሃላፊነት እንደሚያነሱ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ፎቶ – በኤል ሞጃሂድ