‹‹ አዲስ አበባ የመጣነው ጨዋታውን አሸንፈን ለአፍሪካ ዋንጫው ማለፋችንን ለማረጋገጥ ነው ›› ያሲን ብራሂሚ

የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን የምድብ መሪነቱን ያሰፋበትን ውጤት ባለፈው አርብ ኢትዮጵያን 7-1 በመርታት ካሰመዘገበ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚያስገባውን ትኬት ለመቁረጥ በማለም አዲስ አበባ ላይ ዋልያዎቹን ይገጥማል፡፡ ከአርቡ ጨዋታ አንጻር በርካቶች አልጄርያ በቀላሉ ጨዋውን እንደምታሸንፍ ቢገምቱም የቡድኑ ኮከብ ያሲን ብራሂሚ የአዲስ አበባው ጨዋታ ከብሊዳው የተለየ እንደሚሆን ለካፍ ኦንላይን ፍራንስ ተናግሯል፡፡

‹‹ ይህ የተለየ ጨዋታ ነው፡፡ በእግርኳስ ጨዋታ አንደኛው ጨዋታ ከሌላኛው ጋር ሊመሳሰል አይችልም፡፡ ጉዟችን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በአዲስ አበባ ያለው ወበቃማ የአየር ሁኔታ እና ከፍታ ያስቸግረናል፡፡ ነገር ግን ልዩነት ለመፍጠር እና አሸንፈን ወደ ሃገራችን ለመመለስ እንጫወታለን፡፡›› ሲል አስተየቱን የሰጠው ብራሂሚ ለኤል ሞጃሂድ በሰጠው አስተያየትም በአፍሪካ እግርኳስ ከሜዳ ውጪ መጫወት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግሯል፡፡

‹‹ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ሁሉ በኢትዮጵያም ምን እንደሚጠብቀን እናውቃለን፡፡ በአፍሪካ ከሜዳ ውጪ መጫወት ከባድ ነው፡፡ በተለይም የአየር ንብረቱ አስቸጋሪ ነው፡፡ እኛም ይህን ተረድተን ከኢትዮጵያ አዎንታዊ ውጤት ይዘን በመመለሰ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏችንን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡ ››

ጳጉሜ 2006 ላይ በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አልጄርያ ኢትዮጵያን በአአ ስታድየም 2-1 ስትረታ አንድ ግብ ያስቆጠረው የ2015 የቢቢሲ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ያሲን ብራሂሚ ከአዲስ አበባ በድል መመለስ እንደሚገባቸው ገልጧል፡፡

‹‹ በትኩረት በመጫወትና አርብ ምጽ ያሳየነውን አቋም በመድገም ጨዋታውን አሸንፈን መመለስ አለብን፡፡ የአርብ እለቱን አቋም መድገም ከባድ ቢሆንም ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት የምንችለውን ማድረግ ይገባናል፡፡›› ብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *