ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

ከሦስት ሳምንታት ዕረፍት በተመለሰው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ26ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ክለብ ነክ ጉዳዮች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።

👉 ጡዘት ላይ የደረሰው የዋንጫ ፉክክር

ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በደረሰው የሊጉ ውድድር የዋንጫ ፉክክሩን ይበልጥ አጓጊ የሚያደርጉ ውጤቶች በዚህኛው ሳምንት የተመዘገቡ ሲሆን በዚህም መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ሲጥል ተከታዩ ፋሲል ከነማ ደግሞ ድል በማድረግ የነጥብ ልዮነቱ ይበልጡኑ የተጠበበት ውጤት ተመዝግቧል።

በጨዋታ ሳምንቱ መርሐግብር መሰረት ቀደም ብለው የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመውረድ ስጋት ካንዣበበት ባህር ዳር ከተማ ብርቱ ፉክክር የገጠማቸው ሲሆን በዚህም ጨዋታቸውን ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ለመፈፀም ተገደዋል። በእንቅስቃሴ ረገድ በጨዋታው በአጠቃላይ ፈረሰኞቹ እንደቀደሙት ጨዋታዎች በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የነበራቸው አፈፃፀም እምብዛም ውጤታማ ያልነበረ ሲሆን በጨዋታው ከተወሰኑ ቅፅበቶች ውጪ ቡድኑ ለተጋጣሚው ስጋት የሚደቅን አይመስልም ነበር።

በጉዳት ምክንያት ባለፉት ሳምንታት ክፉኛ ሳስቶ የነበረው የጊዮርጊስ የአጥቂ መስመር በባህር ዳሩ ጨዋታ አቤል ያለውን ከጉዳት መልስ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ያገኘ ሲሆን ሌላኛው ለረጅም ጊዜያት ከሜዳ ርቆ የነበረው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ዳግም ወደ ጨዋታ ዕለት ስብስብ መመለሱ ምናልባት ከውጤቱ ባሻገር የሚነሳ አውንታዊ ጉዳይ ነበር ማለት ይቻላል። በአንፃሩ በውድድር ዘመኑ እስካሁን 10 ግቦችን ብቻ በማስተናገድ የሊጉ ጠንካራ የመከላከል መስመር ባለቤት የሆነው ቡድኑ የባህር ዳሩ የሁለት አቻ ውጤት በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአንድ ጨዋታ ከአንድ በላይ ግብ ያስተናገደበት የመጀመሪያ ጨዋታ ሆኖ እንዲያልፍ አድርጓል።

በተመሳሳይ በመጀመሪያው ዙር ከ3ኛ እስከ 5ኛ የጨዋታ ሳምንት በተከታታይ ነጥብ ከተጋሩባቸው እንዲሁም በተመሳሳይ በአንደኛው ዙር መገባደጃ እንዲሁ በሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ነጥብ ከተጋሩ በኋላ በተሻለ ወጥነት ውጤት እያስመዘገቡ የነበሩት ፈረሰኞቹ በሁለተኛው ዙር ሊጉ ከመቋረጡ አስቀድሞ ያለመሸነፍ ጉዟቸው ሲገታ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከባህር ዳር ጋር ነጥብ ለመጋራት የመገደዳቸው ነገር ደጋፊውን በተወሰነ መልኩ ስጋት ውስጥ የሚከት ሲሆን በሰሞነኛ ጨዋታዎች ላይ በተመሳሳይ በእንቅስቃሴም እንደ ቀደመው ጊዜ የበላይነቱን ለማሰየት እየተቸገረ መምጣቱ ለዋንጫ ፉክክሩ ስኬት አሳሳቢ ያደርገዋል።

በተመሳሳይ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በተለይ በመጀመሪያ ዙር እጅግ ወጣ ገባ የሆነ የውድድር ዘመንን ያሳለፉት ፋሲሎች ቀስ በቀስ ውጤታቸውን በማሻሻል አሁን ላይ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ሁነኛ ተፎካካሪ ለመሆን በቅተዋል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በበርካታ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እየታመሱ ከሚገኙት ሰበታ ከተማዎች ብርቱ ፈተና ቢገጥማቸውም በያሬድ ባየህ ብቸኛ የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለውን ድል አስመዝግበዋል።

በጨዋታው እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ምንም እንኳን የተሻለ የማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ያስተዋልናቸው ፋሲሎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች እና በሁለተኛው አጋማሽ በርከት ላሉ ደቂቃዎች በሰበታ ከተማዎች ጫና ስር ቢወድቁም ወሳኙን ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ግን በቅተዋል።

በዚህ ከእንቅስቃሴ በላይ ውጤት ወሳኝ በሚሆንበት የሊጉ ምዕራፍ ላይ እንደመገኘታችን እና በቀሪ አራት የሊግ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ እና ዐፄዎቹ ምንም ዓይነት ስህተት መፈፀም ዋንጫ ማግኘት እና ማጣታቸው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ስለሚኖረው በቀጣይ ጨዋታዎች ስህተቶችን ቀንሶ የተሻለ ውጤት ማስመዘገብ የቻለው ቡድን የሊጉን ክብር ያሳካል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላኛው ትኩረትን የሚስበው ጉዳይ ከመርሐግብር ጋር ተያይዞ የዚህኛው ሳምንትን ጨዋታ ጨምሮ የመጨረሻ ጨዋታ ሳምንትን ሳይጨምር በሚኖሩ ቀጣይ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት በሙሉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታቸውን ከፋሲል ከነማ ቀደመው የሚያደርጉ ይሆናል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ቀድመው የሚጫወትቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ሆኑ የተቀናቃኛቸውን ውጤት ሰምተው ወደ ሜዳ የሚገቡት ፋሲል ከነማዎች ውጤቶቹን እና ሁኔታዎችን ተከትሎ ለሚፈጠሩ አዕምሯዊ ጉዳዮች የሚኖራቸው ግብረ መልስ ይጠበቃል።

👉 ደመወዝ ለመክፈል የተቸገሩት ክለቦቻችን

ሰበታ ከተማ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች አሁንም መታመሳቸውን ቀጥለዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ታድያ ከእነዚህ ቡድኖች ውጤት መጠበቅ ጤናማ ነውን ?

በሀገሪቱ የክለቦች እግርኳስ በትልቁ እርከን ከሚገኙ 16 ክለቦች ውስጥ ለቡድን አባላት ወርሃዊ ክፍያዎችን ያለመቆራረጥ እየፈፀሙ የሚገኙ ክለቦች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ እየሆነ መጥቷል። ይህም ጉዳይ በጣም እየተለመደ ከመምጣቱ የተነሳ አነጋጋሪ የሚሆነው አለመክፈላቸው ሳይሆን የምን ያህል ወራት ሳይከፍሉ ቆይተዋል የሚለው ጉዳይ ሆኗል።

በዚህ ረገድ በጣም አስገራሚ ትዕይንቶችን ያስመለከተን በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ነበር። 21 የቡድኑ ተጫዋቾች ከሦስት ወር ለሚልቅ ጊዜ የደመወዝ ክፍያ አልተፈፀመልንም በሚል ባለፉት ሦስት ሳምንታት ልምምድ አቁመው የሰነበቱ ሲሆን አሰልጣኞች ለቀሪ አምስት ጨዋታዎች ቡድኑን በጣት በሚቆጠሩ ተጫዋቾች ብቻ ሲያዘጋጁ ቆይተዋል።

ታድያ ከቀናት በፊት የፌደሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በተጫዋቾች እና በክለቡ መካከል ያለው ልዩነት እንዲፈታ የቀነ ገደብ በማስቀመጥ የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተሟላ ስብስብ ልምምድ ሳይሰሩ በፋሲል ከነማ ከተረቱበት ጨዋታ መጀመር ጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ በተለያዩ በረራዎች ወደ ባህር ዳር ከተማ አቅንተው ጨዋታ ለማድረግ ተገደዋል።

በተመሳሳይ 30 የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች ከሁለት ወር የሚልቅ ደመወዝ አልተከፈለንም በሚል ከወላይታ ድቻው ጨዋታ አስቀድሞ በነበሩ አምስት ቀናት ልምምድ ሳይሰሩ ቆይተው ጨዋታ ለማድረግ ተገደዋል። ምንም እንኳን በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ አሸንፈው መውጣት ቢችሉም የቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ለወትሮው ከሚያሳየው ብልጫ አንፃር ሲታይ ከልምምድ ስለመራቃቸው የሚጠቁም ነበር።

ሌላኛው ያለፉትን ቀናት በቀውስ ውስጥ ያሳለፈው ክለብ ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ነው። ወልቂጤዎች በተመሳሳይ እንዲሁ ልምምድ ለመጀመር ካቀዱበት ቀን አንፃር በአስራ ሁለት ቀናት ዘግይተው ከዕቅዳቸው ውጪ ለሦስት ቀናት ብቻ ሰርተው ወደ ውድድር የገቡ ሲሆን በዚህም ከመከላከያ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ታድያ ከላይ የጠቀስናቸው ክለቦች ጉዳይ አደባባይ ላይ ስለተሰጣ ብቻ ሳይሆን እንዲሁ መፍትሔ ባላገኙ የፋይናንስ ጥያቄዎች ውስጥ ሆነው በጊዜያዊ ማስታገሻ ብቻ ህይወታቸውን እያስቀጠሉ ያሉ ክለቦች ቁጥር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በመሆኑም የክለቦቻችን የፋይናንስ ምንጭ ፣ አጠቃቀም እና የሀብት አስተዳደር አሁንም በደንብ መፈተሽ ይገባዋል።

በመፍትሄ ደረጃ በርከት ያሉ ሀሳቦች ሲሰነዘሩ ቢቆይም አሁንም ቢሆን በዋነኝነት ክለቦች የፋይናንስ ምንጫቸውን ከመንግሦት ቋት እንዲላቀቅ በማድረግ ሆነ የሚገኝ ሀብትን ደግሞ ከአላዋቂነት ተላቀው በተጠና እና ዘላቂ በሆነ የፋይናንስ አጠቃቀም ስርዓት ወደ መጠቀም ካልመጣን በቅርቡ “የሚባል ክለብ ነበር” ወደ መባል የሚቀየሩ ክለቦች ቁጥር ቀላል አይደለም። የውድድሩን ደረጃ ከፍ ከማድረግ አኳያ ከተመለከትነውም አክሲዮን ማህበሩ ቢያንስ ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ ክለቦች ዓመቱን ለተቀጣሪዎቻቸው ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም የሚበቃ በጀት ስለመያዛቸው ማረጋገጥ የሚችልበት አሰራር ሊኖረው የግድ ይላል። ያ ካልሆነ ግን የቀጥታ ስርጭት ያገኘው የሀገሪቱ ትልቁ የእግርኳስ ውድድር በራሱ ትዝብት ላይ ሊወድቅ ይችላል።

👉 ተመርቶም ቢሆን እያሸነፈ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡናዎች በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አስቀድመው ግብ ቢያስተናግዱም በሁለቱም ጨዋታዎች ከመመራት ተነስተው ድል የማድረጋቸው ነገር በመልካምነቱ የሚነሳ ነው።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ገና ከጅምሩ በ2ኛው ደቂቃ ግብ ያስተናገደው ቡድኑ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመግባት በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ጨዋታውን አሸንፈው በመውጣት ነጥባቸውን ወደ 40 በማሳደግ ወደ ሰንጠረዡ አናት ከፍ ያሉበትን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ይህ ሂደት በተመሳሳይ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በነበረው የመጨረሻ የሊጉ በሀዋሳ ከተማ ሲመሩ ቢቆዩም ውጤቱን ቀልብሰው 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። በሁለቱም ጨዋታዎች ቡድኑ ምንም እንኳን አስቀድሞ ግብ ቢያስተናግዱም መጫወት ከሚፈልጉበት የጨዋታ መንገድ ሳይወጡ ውጤቶችን ለመቀልበስ የሚያሳዩት መታተር እና ይህንን የማድረግ አቅማቸው አድናቆት የሚቸረው ነው። ከዚህ ቀደምም ድራማዊ በሆነ መልኩ ወልቂጤ ከተማን ከመመራት ተነስተው 4-3 ያሸነፉበት ሂደት እንዲሁ የሚታወስ ነው።

እንደ ቡድን ካለው መሻሻል ባለፈ በግለሰቦች ደረጃ የሚታዩ መሻሻሎችን መመልከት ጀምረናል። በተለይም የተከላካይ አማካዩ አብነት ደምሴ ፣ የመስመር ተከላካዩ ያብቃል ፈረጃ እና የመስመር አጥቂው አላዛር ሽመልስ ከጨዋታ ጨዋታ በሚታይ መልኩ የብቃት ደረጃቸው ከፍ እያለ ይገኛል። በዚህም እነዚህ ተጫዋቾች ለቡድኑ ውጤት ማማር ዓይነተኛ ሚናን እየተወጡ ይገኛሉ። ይህ የቡድኑ አዲስ ባህሪ ከዘገየ መምጣቱ በሊጉ የሚያመውን ውጤት እንዲያገኝ ላይረዳው ቢችልም የሦስተኛነት ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ግን ሊያበቃው እንደሚችል ይገመታል።

👉 አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ተያይዘዋል

በእርግጥ በእግርኳስ የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ መተንበይ አስቸጋሪ ቢሆንም በአሁናዊ የሰንጠረዡ አቀማመጥ መነሻነት ከሦስቱ ወራጅ ቡድኖች መካከል የተለየ ተዓምር እስካልተፈጠረ ድረስ የሁለቱ ነገር በተወሰነ መልኩ ፍንጭ የሰጠ ቢመስልም የሦስተኛውን ወራጅ ቡድን ግን በተለይ ከዚህ ሳምንት ውጤቶች በኋላ ይበልጥ አጓጊ የሆነ ይመስላል።

ገና ቡድኖች ማሳካት የሚችሏቸው አስራ ሁለት ነጥቦች ቢቀሩም ሦስተኛው ወራጅ ላለመሆን ግን የሚደረገው ትንንቅ እያየለ መጥቷል። እርግጥ በሂሳባዊ ስሌት መሰረት እስከ በ3ኛ ደረጃ ላይ እስከሚገኘው ሲዳማ ቡና ድረስ ያሉ ቡድኖች የመውረድ ዕድል ያላቸው ቢመስልም ከሁኔታዎች ትንተና ተነስተን ግን ስጋት ያለባቸውን ቡድኖች ጠበብ አድርገን ብንመለከት የአዲስ አበባ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ስጋት ትንሽ የሚያይል ይመስላል።

ላለመውረድ እየተፋለሙ ከሚገኙት ክለቦች መካከል ቀጥተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኙት አዲስ አበባ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻን እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች የተመዘገቡት ውጤቶቹ ጡዘቱን ይበልጥ የጨመሩ ሆነዋል።

አዲስ አበባ ከተማዎች ወላይታ ድቻን በገጠሙበት የረቡዕ ምሳ ሰዓት መርሐግብር ከወትሮው በተለየ ይበልጥ በጥንቃቄ ለመጫወት የሞከሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ነጥብ ተጋርተው ወጡ ተብለው ሲጠበቁ በ92ኛው ደቂቃ ላይ ብዙዓየሁ ሰይፈ ባስቆጠራት ግብ ትልቅ ዋጋ ያለው ሦስት ነጥብ በስተመጨረሻም ይዘው መውጣት ችለዋል። በተመሳሳይ በረቡዕ የቀትር መርሐግብር የአዲስ አበባ ከተማን ማሸነፍ ሰምተው ወደ ሜዳ የገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ፍፁም የበላይነት በተወሰደባቸው ጨዋታ የ3-1 ሽንፈት ለማስተናገድ ተገደዋል።

ውጤቶቹን ተከትሎ በመሩባቸው ጨዋታዎች ውጤት የማስጠበቅ ደዌ የተጠናወታቸው አዲስ አበባ ከተማዎች በቀደሙት ጨዋታዎች በመጨረሻ ደቂቃ ግቦች ነጥብ ሲጥሉ ቢቆዩም በዚህኛው ሳምንት ግን ተቸግረው በሰነበቱበት መንገድ ባስመዘገቡት ድል መነሻነት ነጥባቸው 28 ያደረሱ ሲሆን በአንፃሩ የወጥነት ጥያቄ የሚነሳባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ከሦስት አውንታዊ ውጤቶች በኋላ መሸነፋቸውን ተከትሎ በነበሩበት 29 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በአንድ ነጥብ ተራርቀው በሊጉ 13ኛ እና 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማዎች መነቃቃት ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥሙ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በዚህ ሳምንት ድል ያስመዘገበው አርባምንጭ ከተማን የሚያስተናግዱ ይሆናል። በመሆኑም በቀጣይ ሁለቱ ቡድኖች በሚያስመዘግቡት ውጤት መነሻነት ይዘው የሚያጠናቀቁት ደረጃ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ በጉልህ የሚጠበቅ ይሆናል።

👉 በአጥቂዎቹ ጥረት ከድል የታረቀው ሀዋሳ ከተማ

በአንድ ወቅት የዋንጫ ተፎካካሪ ይመስሉ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ19ኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማን ከረቱበት ውጤት ወዲህ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ድሬዳዋ ከተማን በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል።

በውጤት ረገድ ወልቂጤን ከረቱበት ጨዋታ በኋላ በነበሩት ጨዋታዎች በተጋጣሚዎቻቸው ፍፁም የሆነ የበላይነት ተወስዶባቸው ያስመዘገቧቸው ሽንፈቶች ቡድኑ በብዙ መመዘኛዎች እንዴት እየተፍረከረከ እንደመጣ የሚያሳዩ የነበሩ ሲሆን ከአህጉራዊ ውድድሮች መልስ ግን ሀዋሳ ፍፁም ተነቃቅቶ ተመልክተነዋል።

ጉልበት የጨረሰ ይመስል የነበረው ቡድኑ ከአህጉራዊ ውድድሮች መልስ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ሲረታ በጉልበት ደረጃ ታድሶ ተመልክተነዋል። ጥንቃቄን መርጠው በፈጣን ሽግግሮች ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት ሀዋሳ ከተማዎች በዚህ ሂደት በተለይ ኤፍሬም አሻሞ እና ብሩክ በየነ የነበራቸው መናበብ ባለ ድል አድርጓቸዋል።

በጨዋታው ድንቅ ጥምረት የፈጠሩት ሁለቱ ተጫዋቾች በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ውስጥ ሁለቱ ማለትም 24ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ ኤፍሬም ላስቆጠራት ኳስ እንዲሁም በ65ኛው ደቂቃ ላይ በተቃራኒው ብሩክ ያስቆጠረውን ኳስ ኤፍሬም አመቻችተው ማቀበል የቻሉ ሲሆን በ51ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ ያስቆጠራት ግብ የማጥቃት መነሻም ኤፍሬም አሻሞ ነበር።

ሀዋሳ ከተማዎች ፋሲል ማሸነፉን ተከትሎ አሁን ላይ ወደ አህጉራዊ ወድድር የመመለስ ህልማቸው ሙሉ ለሙሉ ቢያከትምም በቀጣይ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት በመሰብሰብ አሁን ከሚገኙበት የ5ኛ ደረጃ የተሻለ ደረጃን ይዘው ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።