ኢዮብ ዓለማየሁ ቅጣት ተላለፈበት

የጅማ አባ ጅፋሩ የመስመር አጥቂ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ የማይመልሰው ቅጣት ተላልፎበታል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የበላይ አካል የሆነው አክሲዮን ማኅበር በትናንትናው ዕለት በተገባደዱት የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ተከስተዋል ባላቸው የዲስፕሊን ግድፈቶች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል። በካርድ ጥፋቶች ውሳኔ ከተላለፈባቸው ተጫዋቾች ውጪ ደግሞ የጅማ አባ ጅፋሩ የመስመር አጥቂ ኢዮብ ዓለማየሁ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ የማይመልሰው ውሳኔ እንደተላለፈበት ይፋ ሆኗል።

አክሲዮን ማኅበሩ በገፆቹ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ጅማ አባ ጅፋር ከ ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ በ21ኛው ደቂቃ ከዳኛ እይታ ውጭ የተጋጣሚ ተጫዋችን በቁጣ አድራጎት በመራገጡ ከሜዳ መወገድ እንደነበረበት በዕለቱ የጨዋታ ታዛቢ ሪፖርት ቀርቦበት ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መሰረት 4 ጨዋታ እንዲታገድ እና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 እንዲከፍል ተወስኗል።