የሊጉ አክሲዮን ማህበር የጌታነህ ቅጣት የተነሳበትን ውሳኔ እየተለመለከተው ነው

በትናትናው ዕለት የፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ የጌታነህ ከበደን ቅጣት የሻረበትን ሁኔታ አስመልክቶ የፕሪምየር ሊጉ አክስዮን ማህበር ምላሽ ሊሰጥ ነው።

በ25ኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ ወልቂጤ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር 1-1 ከተለያየበት መርሐ ግብር ፍፃሜ በኋላ የወልቂጤ ከተማው አምበል ጌታነህ ከበደ በዳኞች ፣ በጨዋታው ታዛቢ እና የሊጉ አወዳዳሪ አካል ላይ ያልተገባ ዘለፋን ሰንዝሯል በሚል በጨዋታው ኮሚሽነር በቀረበበት ሪፖርት መነሻነት ሦስት ጨዋታ መቀጣቱ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ጌታነህ ከበደ የተወሰነበት ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት ለፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የቅሬታ ደብዳቤን ያስገባ ሲሆን የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውም ጉዳዩን በድጋሚ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ እንዲያጤነው መርቶታል። የዶሲፕሊን ኮሚቴውም ሁኔታውን ከመረመረ በኋላ ‘ተጫዋቹ በጨዋታ አመራሮች ሪፖርት አልቀረበበትም በኮሚሽነር ሪፖርት ብቻ ሊቀጣ አይገባውም’ በማለት ቅጣቱን በትናትናው ዕለት አንስቶለታል።

የውድድሩ የበላይ አካል የሊጉ አክስዮን ማህበር የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ የፌዴሬሽኑን ዲሲፒሊን ኮሚቴ ውሳኔን ተከትሎ ከአራት ሰዓት ጀምሮ ስብሰባ ተቀምጧል። ውሳኔው የተሻረበትን አግባብነት እየመረመረ የሚገኘው ኮሚቴው ምን አልባትም ከሰዓታት በኋላ በሚያወጣው ደብዳቤ የፌዴሬሽኑ የዶሲፒሊን ኮሚቴ የወሰነው ውሳኔ ከህግ አንፃር አግባብነት የጎደለው መሆኑን እና ውሳኔው ሲወሰን በሊጉ የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ውስጥ የራሱ የፌዴሬሽኑ አንድ ተወካይ በተገኘበት የተወሰነ ውሳኔ በመሆኑ እና ከጨዋታ አመራሮች በቂ ሪፖርት ቀርቦበት ውሳኔው መተላለፉን በመግለፅ ለፌዴሬሽኑ የምላሽ ደብዳቤ በመፃፍ ቅጣቱ መሻር የለበትም የሚል አቋም ሊይዝ እንደሚችል ፍንጮች አሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃዎች የምናገኝ ሲሆን ወደ እናንተ የምናደርስ መሆኑን እንገልፃለን።