ኢትዮጵያዊቷ አርቢትር በአፍሪካ ዋንጫ እንድትዳኝ ተመረጠች

ከ15 ቀናት በኋላ የሚጀምረው የእንስቶች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በአርቢትርነት እንዲሳተፉ ከተመረጡ ዳኞች መካከል ሊዲያ ታፈሰ ተካታለች።

ከሰኔ 25 ጀምሮ ለሦስት ሳምንታት በሞሮኮ የሚከናወነው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በ12 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል እንደሚደረግ ይታወቃል። በራባት እና ካዛብላንካ በሚከናወነው ውድድር ላይ በአርቢትርነት የሚሳተፉ ዳኞችን ደግሞ የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍ ይፋ አድርጓል።

በዚህም በውድድሩ 16 ዋና፣ 16 ረዳት እንዲሁም 8 የምስል እገዛ የሚሰጡ ዳኞች ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መመረጣቸው ታውቋል። በዋና ዳኝነት ዝርዝር ከተቀመጡት ስሞች ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያዊቷ ሊዲያ ታፈሰ ስም ይገኝበታል።

በእንስቶች ዘርፍ የአህጉሪቱ ትልቁ ውድድር በሆነው ፍልሚያ ላይ ከአንደኛ እስከ አራተኛ የሚወጡ ብሔራዊ ቡድኖች በቀጣዩ ዓመት በአውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ አዘጋጅነት በሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ትኬታቸውን እንደሚቆርጡ ይታወቃል።

በመድረኩ እንድትዳኝ የተመረጠችው ሊዲያ በፈረንሳይ እግር ኳስ ማኅበር አዘጋጅነት የተከናወነውን የማውሪስ ሪቪሎ ውድድር ለመምራት ያለፉትን ቀናት ፈረንሳይ ነበረች። አልቢትሯ በደቡብ ፈረንሳይ በአስራ ሁለት ሀገራት መካከል ሲደረግ ከነበረው ውድድር ጃፓን ከአልጄሪያ እንዲሁም ከአርጀንቲና ጋር ያደረገችውን ጨዋታ የመራች ሲሆን ባሳለፍነው ማክሰኞም ወደ ሀገር ቤት ተመልሳለች። ከቀናት በኋላ ደግሞ ወደ ሞሮኮ ጉዞዋን የምታደርግ ይሆናል።