የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 0-1 ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ በደንብ የተጠጉበትን ድል ካስመዘገቡበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

አሰልጣኝ ሀይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለጠበበው የነጥብ ልዩነት …?

“እኛ እሱን ሳይሆን የምናየው ፊት ለፊት ያሉትን ጨዋታዎች ማሸነፍ ነው እንጂ ጊዮርጊስ አይደለም፡፡ ከፊት ለፊት የምታገኘውን ጨዋታዎች እያሸነፍክ መሄድ ነው፡፡”

ጠንካራ ሆኖ ስለቀረበው ሰበታ ከተማ…?

“እውነት ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ ነገሮች ናቸው፡፡ አርፎ የመጣ ፣ በውዝግብ የሚመጣ ቡድን ያስቸግራል እና ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን ጠብቀነው ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ማሸነፍ ነው ዋናው፡፡”

ከወትሮው ለየት ስላለው የጨዋታ አቀራረብ እና ስለኦኪኪ በመስመር መሰለፍ…?

“ብሔራዊ ቡድን የነበሩ ተጫዋቾች ትንሽ እረፍትም ማግኘት ስለነበረባቸው ይሄንን መጠቀም ነበረብን፡፡ ስለዚህ ኦኪኪም ከዚህ በፊት እዛው ቦታ ላይ ነው ይጫወት የነበረው። እንቅስቃሴው ብዙም ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ፤ ጥሩ ነበር፡፡ ከእዛ በኋላ አማካይ ላይ ስንሳሳ ሙጂብ ሁለገብ ተጫዋች ነው። አማካይም ይሆናል ፤ አልፎም በረኛ ብታደርገው መጫወት የሚችል ተጫዋች ስለሆነ እሱን ወደ ኋላ መለስ አድርገን ኦኪኪን እንዲረዳው አድርገን በዚህ መልኩ ተጫውተናል፡፡”

ዋንጫ ስለ ማንሳት ዕድል…?

“እኛ ከፊታችን የምናገኘውን ጨዋታዎች እያሸነፍን መሄድ ነው፡፡ ከዛ በኋላ እግዚአብሔር ያለውን መቀበል ነው፡፡ እያንዳንዱ ለእኛ ወሳኝ ጨዋታ ነው፡፡ እያሸነፍክ ጠንክረህ እየተጠነቀክ መሄድ ነው፡፡”

አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ

ሜዳ ላይ ስለነበረው አስደናቂ ቡድን…?

“ተጫዋቾች ላይ የሰራነው የጭንቅላት ስራ ነው፡፡ ሜዳ ከገባችሁ ሁሉንም ነገር ረስታችሁ ፣ ማድረግ የሚገባችሁን አድርጉ የሚለውን ተነጋግረን ስለገባን ተጫዋቾቹ ጥሩ ነገር ሰጥተው ነው የወጡት። ጥሩ ነው እንቅስቃሴያቸው፡፡”

በመልሶ ማጥቃት ስለመጫወታቸው…?

“አንዳንድ ጊዜ ያለህን አቅም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ያለ ልምምድ ሀያ አምስት ቀን ቆይተህ ወደ ሜዳ ስትገባ ወደ ራስህ ጠቅጠቅ ብለህ ኳሱን በያዝከው ጊዜ እየተጫወትክ ወጥተህ አደጋዎችን ፈጥረህ የምታገኛቸውን ውጤት ማግኘት ነው፡፡ ግብ እንዳይገባብህ የሆነ ስራ መስራት ነው፡፡ ይሄንን ስራ ሰርተናል። ነገር ግን በትልቅ ቡድን ተቆጥሮብን በአንድ ጎል ተሸንፈናል።

ስለመከላከል ጥንካሬያቸው…?

“ጨዋታውን በትክክል ለማስኬድ መሀል ላይ ቢያድግልኝ፣ ጅብሪል እና አንተነህ ነበሩ። እነዚህ ልምድ ያላቸው ስለሆኑ የጨዋታውን ሚዛን ወደፊትም ወደኋላም እንዲሄድ የማድረጉን ስራ ስለሰጠናቸው በተሻለ መልኩ ትንሽ ስራን ሰርተዋል ብዬ አስባለሁ፡፡”

ተስፋዎች ይኖራሉ…?

“በዚህ አይነት ሂደት ላይ ይሄን ያህል ሰፊ ተስፋ አለን ብለን የምንጠብቀው ባይሆንም የእግር ኳስ ሂደት ደግሞ ሶስት ብታሸንፍ ሌላው ደግሞ ተሸንፎ ሊጠብቅህ ስለሚችል እግር ኳስን በእግር ኳስነቱ ይዘህ ትጠብቅና ትጫወታለህ፡፡”