ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ከድል ጋር ሲታረቅ የጅማ አባ ጅፋር መጨረሻ ቀርቧል

በሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች ከመመራት ተነስተው ጅማ አባ ጅፋርን ሲረቱ የጅማ በሊጉ የመቆየት ነገር ወደ መጨረሻው ተጠግቷል።

ጅማ አባ ጅፋሮች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በሲዳማ ቡና ከተረታው ስብስብ ላይ ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች አካሉ አታሞ ፣ በላይ አባይነህ እና ዳዊት እስጢፋኖስን አስወጥተው በምትካቸው የዓብስራ ሙሉጌታ ፣ ሱራፌል ዓወል እና ቦና ዓሊ ሲተኩ በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ከመከላከያ አቻ የተለያየውን ስብስብ ሳይለውጡ በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።

እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ወላይታ ድቻዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ሲሆን እንደ ባለፈው የመከላከያ ጨዋታ ሁሉ የተነጠለው አጥቂያቸው ስንታየሁ መንግሥቱ በቂ እገዛ ማግኘት ባለመቻሉ የማጥቃት ጥረታቸው ፍሬያማ መሆን ሳይችል ቀርቷል። ስንታየሁ በአመዛኙ ይበልጥ ወደ ጥልቀት እየመጣ እንዲጫወት በተገደደበት አጋማሽ ቡድኑ በረጅሙ ከኋላ እንዲሁም ከቀኝ መስመር በሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

በአጋማሹ የመጀመሪያው ደቂቃዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ጨዋታውን ለመጀመር የጣሩት እና ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ የግድ ይላቸው የነበሩት ጅማዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሀመድ ከአድናን ረሻድ የተቀበለውን ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ በኋላ በተወሰነ መልኩ ጥንቃቄን የቀላቀለ የጨዋታ መንገድን ለመምረጥ የሞከሩት ጅማዎች ወላይታ ድቻዎች ይበልጥ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ እንዲይዙ የፈቀዱላቸው ቢሆንም ድቻዎች ይህን ቁጥጥር ወደ ጠሩ የግብ ሙከራዎች መቀየር ሳይችሉ አጋማሹ በጅማዎች መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ጉዳት ያስተናገደው መስዑድ መሀመድን አስወጥተው በምትኩ ሙሴ ካበላን በማስገባት የጀመሩት ጅማ አባጅፋሮች ገና ከጅምሮ ነበር ግብ ያስተናገዱት። በ50ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ያሻማውን የማዕዘን ምት ኳስ አበባየሁ አጪሶ በግንባሩ በመግጨት ድቻን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በነበሩ የተወሰኑ ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩ ቢመስልም በሂደት ግን ከጨዋታው የግድ ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸው የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ሲያሳዩ ተመልክተናል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማዎች የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ማስመለስ ቢችሉም የመስዑድ መውጣትን ተከትሎ በኳስ ቅብብል ከሚፈጠሩ ዕድሎች ይልቅ ቡድኑ ወደ ማጥቂያው ሲሶ ሲደርሱ ግን ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ማጥቃት የጀመሩ ሲሆን በዚህም ጥረታቸው እምብዛም ውጤታማ አልነበረም።

በአጋማሹም ምናልባት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መሐመድኑር ናስር ከሳጥን ውጭ ያደረገው እና ቢኒያም ገነቱ ካደናበት ኳስ ውጭ የጠራ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

መሀል ሜዳ ላይ ተገድቦ በቀጠለው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች የጅማ ተጫዋቾች በቁጥር በዝተው ለማጥቃት መሞከራቸውን ተከትሎ ከተከላካይ ጀርባ የሚተውቱን ሜዳ ለማጥቃት ሙከራዎችን አድርገዋል።

በዚህም ሂደት በ86ኛው ደቂቃ ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ የተጣለን ኳስ ስንታየሁ መንግሥቱ ሸርፎ ያቀበለውን ኳስ በአላዛር ማርቆስ እና ተስፋዬ መላኩ አለመናበብ ያገኘውን ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ቢኒያም ፍቅሬ በቀላሉ ገጭቶ በማስቆጠር ወላይታ ድቻን ባለድል ማድረግ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በ41 ነጥብ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ በነበሩበት 23 ነጥብ የቀጠሉት ጅማዎች ቀሪ ሁለት ጨዋታቸውን ቢያሸንፎም በሊጉ የመቀጠል ተስፋቸው በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ነጥብ ማሳካት ላይ የተንጠለጠለ ሆኗል።