የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-2 ወላይታ ድቻ

በ86ኛው ደቂቃ ቢኒያም ፍቅሬ ባስቆጠራት ግብ ወላይታ ድቻዎች የጅማ አባ ጅፋርን በሊጉ የመቆየት ተስፋን አጣብቂኝ ከከተቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

“በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው በፈለግነው መልኩ የሄደ ነበር ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ግን በየ3(4) ቀናት ልዮነት እንደመጫወታችን በምንፈልገው መንገድ እንዳንቀጥል አድርጎናል።”

ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ስላጣው ነገር

“በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ የመስዑድ አለመኖሩን ተከትሎ የምንፈልገውን ነገር ማድረግ አልቻልንም ፤ እነሱ በመልሶ ማጥቃት መጫወት እንደመፈለጋቸው ያንን ስንጠነቀቅ ነበር።”

ስለመስዑድ መሀመድ በሁለተኛው አጋማሽ አለመኖሩ

“በተደጋጋሚ በመጀመሪያው አጋማሽ እሱን ለመጠቀም እንሞክር ነበር ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ እሱን ካጣን ወዲህ ቀይረን ያስገባናቸው ልጆች ያንን ነገር ሊሰጡን አልቻሉም።”

በሊጉ ስለመቆየት ተስፋቸው

“የራሳችንን ስራ እየሰራን የሌሎችን ውጤት እንጠብቃለን።”

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ወደ አሸናፊነት ስለመመለሳቸው

“እግርኳስ ሂደት ነው ፤ ግብ የማስቆጠር ችግራችን አብሮን የቀጠለ ነው እስካሁን መጓዝ የቻልነው በመከላከል አደረጃጀታችን ጥንካሬ ነው በባህርዳር የሊጉ ቆይታ እስካሁን ሁለት ግቦች ብቻ ነው ያስተናገድነው። ተስፋ ሳንቆርጥ ተጫውተን ማሸነፋችን በጣም ጥሩ ነው ከዚህ በላይ ደግሞ ወጣት ተጫዋቾቻችን ግብ ማስቆጠር መቻላቸው አስደስቶኛል።”

ስንታየሁ መንግሦቱን ታሳቢ ስላደረጉ ኳሶች

“እኛ አሁን አየሰራን የምንገኘው የተከላካይ ሆነ የማጥቃት መስመራችን ከመሀል ክፍሉ ነጥለን እየሰራን ነው በዚህ ሂደት በረጃጅም በሚጣሉ ኳሶች ታሳቢ የምናደርገው ስንታየሁን ከእሱ በሚነሱ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ጥረት እናደርጋለን ። በማጥቃት ረገድ ግን በጥቅሉ ተቸግረን ቆይተናል ይህንን ገምግመን በጣም ማሻሻል ይኖርብናል።”

“ዞሮ ዞሮ ጉልበታችንን ቆጥበት በታክቲኩ ረገድ ደግሞ ዲሲፕሊንድ ሆነን በመጫወት ውጤቱን ይዘን ልንወጣ ችለናል ፤ በቀጣይም ለምናደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የተሻለ መነሳሳት ይፈጥርናል ብዬ አስባለሁ።”