‹‹ውጤቱን ዳኛው ወስዶብናል ብዬ ነው የማስበው›› አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ አመሻሽ ከአልጄርያ ጋር ባደረገው ጨዋታ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የእለቱ ዳኛ በውጤቱ ላይ ተፅእኖ መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ በጨዋታው የተሻልን ነበርን፡ በጨዋታው የተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ከዛ ውጪ ግን ቡድኑ ለሰንደቅ አላማውና ለህዝቡ ሲል የሚገባውን አድርጓል፡፡ ከምንም በላይ የተጫወትነውን ጨዋታ ስናይ በተጨማሪም የተሰጠብን ፔናሊቲ ሳስበው ውጤቱን ዳኛው ወስዶብናል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ›› ብለዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ አክለውም በጨዋታው 3 ጊዜ መርተው በአቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው የእግርኳስ አንድ አካል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

‹‹ ይህ የእግርኳስ ጠባይ ነው፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ አንድ ትልቅ ነገር የየነው ተጫዋቾቼ ዛሬ ከምንም በላይ የህዝቡን ድጋፍ በመመልከት ያላቸውን ሁሉ ሰጥተዋል፡፡ ቅድም እንዳልኩት ከተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት ውጪ ቡድኔ ጥሩ ተንቀሳቀሷል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱ በፍፁም አያሳምንም፡፡ ››

PicsArt_1459279213454

በዛሬው ጨዋታ ሁለት ኳሶች ያቀበለው ታደለ መንገሻ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ መውጣቱ ከደጋፊዎች ተቃውሞ ቢያስከትልም አሰልጣን ዮሃንስ ታደለ እየተዳከመ በመምጣቱ ለመቀየር እንደተገደዱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ታደለ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ ቀይሬ ያስወጣሁት በብቃት ችግር ሳይሆን በትንፋሽ በኩል ስለደከመ ነው፡፡ በመስመር በኩል እየተጠቃን ስለነበር ነጥብ ይዞ ለመውጣት መስመሩን ማጠንከር ነበረብን፡፡ ››

አሰልጣኝ ዮሃንስ በአርቡ የ7-1 ሽንፈት ዙርያም ይህንን ብለዋል፡፡

‹‹ ያለፈው ጨዋታ እኮ ከኳስ ውጪ ነው፡፡ ይህንን ተጫዋቾቹም መናገር ይችላሉ፡፡ ረጅም ጉዞ አድርናል፡፡ አንድ ሰው ሃያ ሰአት ሳይተኛ እንዴት ይጓዛል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ አልጄርያን የሚያክል ቡድን መግጠም አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔ ለ7-1 ሽንፈቱ ሙሉ ለሙሉ ሃላፊነት እወስዳለሁ፡፡ ለመጣውም ውጤት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ነገር ግን ከሽንፈታችን ጀርባ ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ በዛሬውም ጨዋታ አንድ ቀን አርፈን ነው የተጫወትነው፡፡ ፊፋ አንድ ቡድን ጨዋታ ካደረገ በኋላ ቢያንስ 48 ሰአት ማረፍ አለበት ቢልም ከ48 ሰአት ውስጥ 20ውን ሰአት በጉዞ ነው ያሳለፍነው፡፡ ተጫዋቾቼ ከዚህ ሁሉ ድካም በኋላ ይህንውጤት በማስመዝገባቸው ትልቅ ክሬዲት ነው የምሰጣቸው፡፡ ›› ያሉት አሰልጣኝ ዮሃንስ ለአፍሪካ ዋንቻው የማለፍ ተስፋቸው እንዳልተሟጠጠም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

‹‹ እንኳን ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዘን ወጥተን ሳናገኝ እንኳን ለጥሩ ሁለተኝነት ከሚወዳደሩት አንዱ ነን፡፡ በሌሎች ምድቦች ከኛ በላይ ነጥብ ያላቸው ጥሩ ሁለተኞች ጥቂት በመሆናቸው አሁንም ለአፈሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋ አለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ከ7-1 ሽንፈቱ በኋላ ከብሄራዊ ቡን ስራቸው በገዛ ፍቃዳቸው ይለቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም አሰልጣኝ ዮሃነስ ሳህሌ ግን በጉዳዩ ዙርያ ብዙ ማውራት እንደማይፈልጉ ገልፀዋል፡፡ ‹‹አሁን ማውራት አልችልም፡፡ በሌለ ነገር ላይ ማውራት አልችልም፡፡ ››

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *