“እርምጃ የማይወሰድበት ወይንም ደግሞ ህጋዊ ነገር የማናደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርም” አቶ ባህሩ ጥላሁን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሀፊ

በሰሞንኛው የእርግኳሱ መነጋገሪያ ጉዳይ ዙሪያ ቀደም ብለን የፋሲል ከነማን እና የሊግ ካምፓኒውን ዕይታ ያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን አስተያየት ተቀብለናል።

የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከትናንት በስቲያ ፍፃሜውን አግኝቷል። በመጨረሻው ሳምንት በተመሳሳይ ሰዓት በተደረጉ ወሳኝ ጨዋታዎች ዙሪያ የተነሳው ውዝግብ ግን እስካሁን እንደቀጠለ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም አዳዲስ ነገሮችን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሦስቱም ጨዋታዎች ላይ ቅሬታዎች የተስሙ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ከፍ ባለ ሁኔታ ስማቸው የተነሱ ክለቦችን እና የእግርኳሱን አስተዳዳሪ አካላት ለማናገር ሞክራለች። ቀደም ሲል ፋሲል ከነማ እና የውድድሩ የበላይ አካል የሆነው የፕሪምየር ሊጉን አክሲዮን ማህበር ሀሳብ ያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ የሀገሪቱ እግርኳስ አስተዳዳሪ የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምልከታን ከተቋሙ ዋና ፀኃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጋር ባደረግነው አጠር ያለ ቆይታ ለመረዳት ችለናል።

በ30ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የተፈጠሩ ክስተቶችን ከሊጉ ባለፈ እንደ ሀገር እግርኳሱ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ብላችሁ ወስድችሁታል ? ወይስ እግርኳሳዊ አጋጣሚ ነው ብላችሁ አልፋችሁታል ?

“ይሄ ነው ማለት ይከብዳል። ምክንያቱም በእግርኳስ ሊፈጠሩ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የመጨረሻ ደቂቃ ድራማዎች ይኖራሉ። ነገር ግን ይሄ ከዛ ውስጥ የሚመደብ ነው አይደለም የሚለውን ግን በደንብ ማየት ያስፈልጋል ፤ ቪዲዮውን መከታተል ያስፈልጋል። እንደዚሁም ደግሞ ኮሚሽነሩ የሚሰጠውን ሪፖርት እና የዳኛ ሪፖርት መመልከት እጅግ በጣም ያስፈልጋል። የእኛ አቋም ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ጨዋታዎችም በዚሁ ደረጃ መታየት ይኖርባቸዋል ብለን እናስባለን። አወዳዳሪው አካል በተመሳሳይ ሰዓት ከማጫወት ውጪ ሌላ ነገር ማድረግ አይችልም። ከዛ ካለፈ በቪዲዮ የማስቀረፅ ሥራዎችን ነው ልታካሂድ የምትችለው ፤ በማስረጃነት ለመጠቀም። በዛ ደረጃ አሁን ፋሲል እና ድሬዳዋ ያደረጉትን ጨዋታ የተፈጠረው ነገር እውነት እንደተባለው እስከ 77ኛው ደቂቃ ተጠብቆ ከዛ በኋላ ባሉት ተከታታይ ጊዜያት ጎሎች የተቆጠሩበት መንገድ ምን ይመስላል ? ከmatch fixing ጋር የተያያዘ ነው ወይ ? የሚለውን ማየት ይጠይቃል። ቪዲዮዎቹንም ማየት ይጠይቃል። ከዛ ውጪ ሪፖርቶችንም በደንብ መከታተል ይፈልጋል። እንደማንኛውም ሰው ስትሰማው ሊያጠራጥር የሚችል ነገር እንዳለ ግን ማየት ይቻላል። እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን በቁም ነገር እኛም የምንመለከተው ይሆናል ማለት ነው።”

የተነሱት ሀሜቶች እንደሀገር እግርኳሱ ላይ ጠባሳ የሚያሳርፉ ናቸው ብሎ ፌዴሬሽኑ ካመነ በጉዳዩ ላይ እጁን ያስገባል ?

“እግርኳሱን በበላይነት የሚመራ አካል እንደመሆኑ መጠን ከሊግ ካምፓኒው ከአወዳዳሪው አካል የሚመጡ ሪፖርቶችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በጉዳዩ ላይ (አዲስ አበባ ከተማም በጉዳዩ ላይ ጥያቄ አቅርቧል) ይሄንንም ጥያቄ የምንመረምር ይሆናል ማለት ነው። ይሄ በትልቁ ማየት የሚገባን ነገር ነው። ሌሎች ሀገራት ላይ የምንሰማቸው ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በጭምጭምታ ደረጃ እንሰማቸው የነበሩ ነገሮች እንዲፈጠሩ አንፈልግም። በቀጣይ የሚደረጉ ውድድሮች ላይ ደግሞ ተፅዕኖው ያርፍባቸዋል። ሁሌ በጥርጣሬ የሚደረግ ውድድር ሊሆን ይችላል። እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንደ በላይ አወዳዳሪ አካል ሊግ ካምፓኒው የሚያቀርበውን ሪፖርት ተመልክቶ እንደፌዴሬሽን የሚለው ነገር ይኖረዋል። ጨዋታው እንደዚህ ዓይነት ክፍተቶች ካሉበት እርምጃ የማይወሰድበት ወይንም ደግሞ ህጋዊ ነገር የማናደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርም።”

በተመሳሳይ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያለውን ሀሳብ ለማግኘት የክለቡን ሥራ አስኪያጅ ለማግኘት ባደረግነው ጥረት ሀሳባቸውን ለመስጠት ሊተባበሩን አልቻሉም። ከዚህ በኋላም ክለቡ የሚሰጠውን ማብራሪያ ካለ ለማስተናገድ በራችን ክፍት መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።