አቡበከር ናስር የጎፈሬ ብራንድ አምባሳደር ሆኖ ነገ ይፈራረማል

ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ የወቅቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ኮከብ አቡበከር ናስር የብራንድ አምባሳደሩ ለማድረግ ነገ ስምምነት ይፈፅማል።

የሀገር ውስጥ የስፖርት ትጥቅ አቅርቦት ጥያቄዎችን በሚገባ እየመለሰ የሚገኘው ግዙፉ ሀገር በቀለ ተቋም ጎፈሬ በሁለቱም ፆታዎች ከዋናው የሀገሪቱ የሊግ እርከን እስከ ታችኞቹ ድረስ አልፎም የጤና ቡድኖችን በልዩ ምርቶቹ እያደመቀ የሚገኝ ሲሆን ከሰሞኑን ደግሞ ትላልቅ ስምምነቶችን እያገባደደ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ አንደኛውን ነገ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ቢሮው ይፋ ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።

የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም መስራች እና ሥራ-አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን ለሶከር ኢትዮጵያ “ባለ-ራዕዩ ተቋም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ትልቅ አሻራ እያሳረፈ የሚገኘው አቡበከር ናስርን ብራንድ አምባሳደር ለማድረግ ተስማምቷል። ነገ በምንሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ስምምነቱን ይፋ እናደርጋለን።” በማለት ሀሳባቸውን ገልፀዋል። የደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሜሎ ዲሰንዳውንስ ንብረት የሆነው አቡበከር ወደ ደቡብ አፍሪካ ከማምራቱ በፊት ነገ 10 ሰዓት ስምምነቱን ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ከተጫዋቹ ጋር የሚደረገው ስምምነት ዝርዝር ጉዳዮች ደግሞ ለብዙሃን መገናኛ አባላት የተዘጋጀው መግለጫ ላይ በስፋት እንደሚገለፅ ተጠቁሟል።