ኢትዮጵያ ቡና ከተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾቹ ጋር በስምምነት ተለያይቷል

ከደቂቃዎች በፊት ከታፈሰ ሰለሞን ጋር መለያየቱን የዘገብነው ኢትዮጵያ ቡና ከተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾች ጋር በተመሳሳይ ለመለያየት ከስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከአማካይ ተጫዋቹ ታፈሰ ሰለሞን ጋር ለመለያየት እንደተስማማ ከተጫዋቹ ባገኘነው መረጃ ከሰዓታት በፊት አስነብበናቹሁ ነበር። አሁን ደግሞ ከመስመር አጥቂዎቹ ሚኪያስ መኮንን እና ዊልያም ሰለሞን እንዲሁም ከተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ ጋር ለመለያየት ስምምነት ላይ እንደደረሰ ሰምተናል። ዊልያም በ2013 ከመከላከያ በብዙ ውዝግብ መልቀቂያ ከወሰደ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን በመቀላቀል በመጣበት ዓመት ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በዘንድሮ ዓመት የደሞዝ እርከኑን ከፍ በማድረግ ለተጨማሪ ሦስት አመት ለማቆየት አዲስ ውል አስሮ እንደነበር ይታወቃል።

ሚኪያስ ደግሞ 2009 ላይ ከሀረር ሲቲ 17 ዓመት በታች ቡድን ቡናማዎቹን ተቀላቅሎ ቆይታን ሲያደርግ የነበረ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ባልተለመደ ሁኔታ ከአቡበከር ናስር ጋር የአምስት ዓመት ውል ፈርሞ የነበረ ቢሆንም ጉዳት እና የአቋም መውረዶች እድገቱን በታሰበው ልክ ሳያደርጉት ቆይተዋል።

በዚህ ዓመት መጀመርያ ከሀዲያ ሆሳዕና ለሦስት ዓመት ለመቆየት ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ የነበረው ቴዎድሮስ በቀለ በበኩሉ የተጠበቀውን ያህል ግልጋሎ ሳይሰጥ ዓመቱን ማሳለፉም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ዊሊያም እና ቴዎድሮስ ሁለት ሚኪያስ ደግሞ ሦስት ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚያቆያቸው ቀሪ ውል ቢኖርም ከክለቡ ጋር በመነጋገር በስምምነት ለመለያየት የተስማሙ ሲሆን ነገ ወደ ፌዴሬሽኑ በማቅናት አራት ሺህ ብር በመክፈል ውላቸውን እንደሚቀዱ ተጫዋቾቹ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል።