የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክርስቲያን ጎርኩፍ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ጋር 3-3 በሆነ ውጤት ጨዋታውን ማጠናቀቁን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት የሜዳው አለመመቸት ጨዋታውን ከባድ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል፡፡ “ሜዳው ለጨዋታ በፍፁም የሚመች አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት እንደፈለግነው መጫወት አልቻልንም፡፡ ውጤቱ ጥሩ ነው እንዳሸነፍን ነው የምቆጥረው፡፡” ብለዋል፡፡
ጎርኩፍ አያይዘውም ለእርሳቸው የጨዋታው ኮከብ የዋልያው አማካይ ታደለ መንገሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የ60 ዓመቱ ፈረንሳዊ ከአልጀሪያ ሚዲያዎች ከባድ ጫና እየደረሰባቸው ሲሆን ስማቸው ከፈረንሳዩ ክለብ ቦርዶ ጋር ደጋግሞ በመነሳት ላይ ይገኛል፡፡ ያም ሆኖ አሰልጣኝ ጎርኩፍ አሁንም የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው መቀጠል እንደሚፈልጉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ “ከቦርዶ የመጣልኝ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለም፡፡ አሁንም የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆን እፈልጋለው፡፡ የመጨረሻ ውሳኔ የአልጄሪያ እግርኳስ ፌድሬሽን ነው፡፡” በማለት ጎርኩፍ ሃሳባቸውን አጠናቅቀዋል፡፡