‹‹እንደ እንቅስቃሴያችን የአቻ ውጤቱ አይገባንም ነበር›› ጌታነህ ከበደ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከአልጄርያ ጋር በተከታታይ ካደረጋቸው ጨዋታዎች በአንዱ ተሸንፎ አንዱን አቻ ወጥቷል፡፡ ቡድኑ አልጄርያ መረብ ላይ ካሳረፋቸው 4 ግቦች ሶቱን ከመረብ ያሳረፈው ጌታነህ በብሄራዊ ቡድኑ የፊት መስመር ተፅእኖ ፈጣሪ መሆኑን በድጋሚ አስመስክሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶርያው አጥቂ በጨዋታዎቹ እና በግል እንቅስቃሴው ዙርያ ዛሬ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

በርካታ ቡድኖች ከአስከፊ ሽንፈት መልስ ቶሎ ለማገገም ይቸገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ7-1 ሽንፈቱ አገግሞ በትላንቱ ጨዋታ ጥሩ እንዲንቀሳቀስ ያደረገው ምስጢር ምንድን ነው?  

ከሽንፈቱ በኋላ ብዙ ነገር አስተካክለናል፡፡ አሰልጣኛችንም ብዙ መክሮናል፡፡ በብሊዳው ጨዋታ ሰባት ጎል ገብቶብናል፡፡ ነገር ግን ምንም አልሆንም፡፡ አዚህም ብንሸነፍ ምንም አንሆንም፡፡ ያንን ተነጋግረን በነፃነት ለመጫወት አእምሮአችንን ዝግጁ አድርገን ነው የገባነው፡፡

የትላንቱ ጨዋታ እንዴት ነበር የአቻ ውጤቱ ጨዋታውን ይገልፀዋል ብለህ ታምናለህ?

ትላንት ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለናል፡፡ በጨዋታው አከሌ እንዲህ ነበር ተብሎ የሚባል ተጫዋች አልነበረም፡፡ ሁሉም ጥሩ ተንቀሳቅሷል፡፡ ነገር ግን እንደ እንቅስቃሴያችን የአቻ ውጤቱ አይገባንም ነበር፡፡

ከጨዋታው በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረግከው ቆይታ ቡድኑ በርካታ አጥቂዋችን በማጣቱ ግብ የማስቆጠር ጫናው በእኔ ላይ ይወድቃል ብለህ ነበር፡፡ ጫናውን ተቋቁሜ ሃላፊነቴን ተወጥቻለሁ ብለህ ታስባለህ?

ሃላፊነቴን በሚገባ ተወጥቻለሁ፡፡ በመጀመርያውም ጨዋታ ተሸነፍን እንጂ እኔም ሆነ የቡድን ጓደኞቼ የምንችለውን አድርገናል፡፡ በሁለቱም ጨዋታ ለቡድኔ የቻልኩትን አድርጌያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ በፊት የማደግረውን ነው አሁንም እያደረግኩ ያለሁት፡፡

PicsArt_1459338080830

በሁለቱም ጨዋታዎች ከአንተ የሚጠበቀውን ማድረግ ችለሃል፡፡ ይህ አቋምህ በክለብህ ፕሪቶርያ ዩኒቨርሲቲ የሚኖርህ ቆይታ ላይ ምን አስተዋፅኦ ያደርጋል?

በሁለቱ ጨዋታ ያሳየሁት አቋም ለአሰልጣኙም መልእክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም በአለም ዋንጫ ማጣርያ ኮንጎ ላ በደርሶ መልስ ግቦች አስቆጥሬ ለአሰልጣኙ መልእክቴን አስተላልፌያለሁ፡፡ የአልጄርያው ጨዋታ ለእግርኳስ ህይወቴ ቀጣይ ምዕራፍ ትልቅ በር ይከፍታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁልጊዜም ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ብዙ እድሎችን ይፈጥራል፡፡ አንድ የእግርኳስ ተጫዋች የሚለፋው ለብሄራዊ ቡን መመረጥ ነው፡፡ እኔም እዚህ የምመጣው ሁኔታው ተመቻችቶልኝ ሳይሆን ለማልያው ካለኝ ፍቅር እና ቀጣይ የሚኖረኝን አድል በማሰብ ነው፡፡

በሁለቱም ጨዋታዎች ግብ ከማስቆጠርህ በተጨማሪ ግቦቹ የአንተን የቦታ አያያዝ እና የአጨራረስ ብቃት ያሳዩ ነበሩ፡፡ ከሌሎች አፍሪካውያን አጥቂዎች ጋር ስታነፃፅረው ራስህን ምን ደረጃ ላይ ታስቀምጠዋለህ?

ራሴን ጨራሽ አጥቂ ነኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡ አልጄርያ ላይ በተደረገውም ሆነ በትላንቱ ጨዋታ ያገኘኋቸውን እድሎች ነው ወደ ግብነት የቀየርኩት፡፡ የማገኛቸውን የግብ አድሎች በአግባቡ ስለምጠቀም ጨራሽ አጥቂ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡

አሁን በምድባችን 2ኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድላችንን እንዴት ታየዋለህ?

ትላንት ብናሸንፍ የተሻለ ነበር፡፡ አሁንም ግን አድላችን አልተሟጠጠም፡፡ ትላንት ብናሸንፍ ኖሮ በእርግጠኝነት የማለፍ እድላችን ይሰፋ ነበር፡፡ በቀጣይ የሚገጥሙን ሌሶቶ እና ሲሸልስን ማሸነፍ ከቻልን የማለፍ እድል ይኖረናል፡፡

PicsArt_1459338039882

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *