አዳማ ከተማ አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለን ዋና አሠልጣኙ አድርጎ ሾመ

የውድድር ዓመቱን በምክትል አሠልጣኝነት ጀምረው በጊዜያዊ ዋና አሠልጣኝነት ያገባደዱት አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ዋና አሠልጣኝ ሆነዋል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፈው አዳማ ከተማ በተጠናቀቀው ዓመት እስከ መጨረሻኛ ሳምንት ድረስ በሊጉ ለከርሞ መኖሩን ሳያረጋግጥ ቆይቶ ነበር። በቀጣይ ዓመት የነበሩበትን ክፍተቶች አሻሽሎ ለመቅረብ ያለመ የሚመስለው ቡድኑ የዋና አሠልጣኙን ጉዳይ በተመለከተ አዲስ ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህም በትናንትናው ዕለት የክለቡ አመራሮች ባደረጉት ስብሰባ አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ቡድኑን በዋና አሠልጣኝነት እንዲመራ ውሳኔ አሳልፈዋል።

በፋሲል ከነማ እና ሰበታ ከተማ በምክትል አሠልጣኝነት ሰርተው ዓምና አዳማን በመቀላቀል ለሦስተኛ ጊዜ ምክትል በመሆን የአሠልጣኝነት ህይወታቸውን የቀጠሉት አሠልጣኝ ይታገሱ ዋናቸው አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከክለቡ ጋር ከተለያዩ በኋላ የመጨረሻዎቹን 6 ጨዋታዎች በጊዜያዊነት ዋና ሆነው መምራታቸው አይዘነጋም።