ዮርዳኖስ ዓባይ የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ሆኗል

ከሰዓታት በፊት ባቀረብነው ዘገባ መሠረት ዮርዳኖስ ዓባይ በይፋ የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ሆኗል።

ድሬዳዋ ከተማ ከአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ጋር በስምምነት መለያየታቸውን እና በምትካቸውም የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ ባደረገው ውይይት አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይን ለአንድ ዓመት ለመሾም እንደተቃረበ ከሰዓታት በፊት መዘገባችን ይታወቃል።

አሁን ክለቡ ይፋ ባደረገው መሠረት አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ድሬዳዋ ከተማን ለማሰልጠን ለአንድ ዓመት መስማማቱን አረጋግጧል። ዮርዳኖስ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ወደ አሰልጣኝነቱ በመግባት በናሽናል ሲሚንት እና ድሬዳዋ ፖሊስ የአሰልጣኝነት ህይወትን የጀመረ ሲሆን ያለፉትን ሁለት አመታት በመከላከያ በምክትል አሰልጣኝነት ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።

በሌላ ዜና ክለቡ የቀድሞ ቡድን መሪውን ቶፊቅን ወደ ቦታው ሲመልስ በተጨማሪም የቀድሞ የክለቡን ሥራ አስኪያጅ አቶ እስከዳርን ወደ ኋላፊነታቸው መመለሳቸውን ሰምተናል።