በ2017 ዛምቢያ ላይ ለሚስተናገደው የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የ1ኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት ይጀምራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ቡድን በመጪው እሁድ ሶማልያን በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያስተናገድ ሲሆን እንግዳው ቡድንም ትላንት ምሽት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
ሶማልያ በአጠቃላይ 27 የልኡካን ቡድን ይዛ በመምጣት አዲሱ ገበያ አካባቢ የሚገኘው ኤስጂኤስ ሆቴል ማረፉ ታውቋል፡፡ ቡድኑ ዛሬ 18 ተጫዋች በመያዝ ረፋድ የመጀመርያ ልምምዱን ያደረገ ሲሆን ቀለል ያሉ የማላቀቅያ እና ከኳስ ጋር ልምምዶች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ አስተናግዳው በነበረው የሴካፋ ውድድር ላይ ለሶማልያ የተጫወቱ አንዳንድ ተጫዋቾችን በዛሬው ልምምድ ላይ ተመልክተናል፡፡
ይህ የማጣርያ ጨዋታ አርብ እንዲካሄድ በካፍ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ ጥያቄ አቅራቢነት እሁድ 10፡00 በአዲስ አበባ ስታድየም ይካሄዳል፡፡