አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል

ስማቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚነሳው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከትውልድ ከተማቸው ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸው ታውቋል።

ከአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ጋር መለያየቱ የታወቀው ኢትዮጵያ ቡና ቀጣዩ የቡድኑ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል። ምንም እንኳን በአሰልጣኙ እና በክለቡ በኩል ይፋዊ የሆኑ ማረጋገጫዎች ባይወጡም የቡናማዎቹ አመራሮች እና አሰልጣኝ ተመስገን ዳና የስልክ ልውውጦችን ያደርጉ እንደነበረ እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ቡና የመጡም ሆነ ከክለቡ ጋር በስምምነት የተለያዩት ተጫዋቾች በአሰልጣኙ ጥቆማ እንደሆነ ተሰምቶ ነበር።

ይህን ግኑኝነት ወደ ውል ስምምነት ለመቀየር እና የስምምነቱን ዝርዝር ሁኔታዎችን ይፋ ለማድረግ በዛሬው ዕለት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከትውልድ ከተማው ሀዋሳ ተነስቶ አዲስ አበባ መግባቱን ለማወቅ ችለናል። አመሻሽ ላይም ከክለቡ የበላይ አካላቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና የቡናማዎቹ ዋና አሰልጣኝ መሆኑ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሀዋሳ ከተማ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖችን በማሰልጠና በርከት ያሉ ተስፈኛ ወጣቶችን ያፈራ ከመሆኑ ባሻገር በከፍተኛ ሊግ በደቡብ ፖሊስ እና የኢትዮጵያ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሲያሰለጠን የቆየ ሲሆን በዘድሮ ዓመት ለአስራ ስምንት ሳምንት ጨዋታዎችን ከወልቂጤ ከተማ ጋር በዋና አሰልጣኝነት መስራቱ አይዘነጋም።