ወጣቱ ግብ ጠባቂ ኢትዮጵያ መድንን ተቀላቅሏል

ኢትዮጵያ መድኖች ግብ ጠባቂ የግላቸው ማድረጋቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች ዛሬ ደግሞ 10ኛ ፈራሚያቸው በማድረግ ወጣቱን የግብ ዘብ አቡበከር ኑራን ለሁለት ዓመት ማስፈረማቸውን አረጋግጠዋል።

ፈጣን እድገት በማሳየት ላይ የሚገኘው ወጣቱ ግብ ጠባቂ የእግርኳስ ህይወቱን በመቱ ከተማ የጀመረ ሲሆን ቀጥሎም በከፍተኛ ሊግ ተካፋይ በነበረው ወሎ ኮምቦልቻ ተጫውቶ ያለፈ ሲሆን ከ2013 አንስቶ ደግሞ በፕሪሚየር ሊጉ ለጅማ አባ ጅፋር እና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ቆይታን አድርጓል።

ግብ ጠባቂው ከባህር ዳር ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል የነበረው ቢሆንም በስምምነት ውሉን በማቋረጥ ወደ ኢትዮጵያ መድን አምርቷል ፤ በመድንም ለቀጣዩቹ ሁለት የውድድር ዘመናት ቆይታ የሚያደርግ ይሆናል።

በገበያው በንቃት እየተሳተፉ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች እስካሁን 10 አዳዲስ ተጫዋቾች ያስፈረሙ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች ተጨማሪ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርሙም ይጠበቃል።