ሀድያ ሆሳዕና የሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

ነብሮቹ በስብስባቸው የሚገኙ ሁለት ተጫዋቾችን ውል አራዝመዋል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቀጣዩ የውድድር ዘመን ላይ ጠንክሮ ለመቅረብ በዝውውር መስኮቱ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና በቀጣዩቹ ቀናት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹን በይፋ በዋና አሰልጣኝነት መንበር ከመሾሙ አስቀድሞ የሄኖክ አርፊጮን ኮንትራት በማደስ የቤዛ መድህን ፣ ዳግም ንጉሴ እና ሰመረ ሀፍታይን ዝውውር ያገባደደ ሲሆን አሁን ደግሞ የሁለት ነባር ተጫዋቾችን ውል ለአንድ ተጨማሪ ዓመት እንዳደሰ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ እና ተጫዋቾቹ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የሀላባ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካይ እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሆኖ ሲጫወት የምናውቀው እያሱ ታምሩ በሀድያ ሆሳዕና ለከርሞው መቆየቱ የተረጋገጠ የመጀመሪያው ተጫዋች ነው። ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ ነው።