ሠራተኞቹ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈርመዋል

አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን የሾሙት ወልቂጤ ከተማዎች የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር አገባደዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 8ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ወልቂጤ ከተማዎች ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ የቀጣይ ዓመት ቡድናቸውን እያዋቀሩ የሚገኝ ሲሆን ከቀናት በፊትም ሳለአምላክ ተገኝ፣ ዜናው ፈረደ፣ አፈወርቅ ኃይሉ እና ቴዎድሮስ ሀሙን ማስፈረማቸውን ዘግበን ነበር። በዛሬው ዕለት ደግሞ ተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን አውቀናል።

ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች አዲስዓለም ተስፋዬ ነው። ለረጅም ዓመታት በሀዋሳ ከተማ ግልጋሎት የሰጠው የመሐል ተከላካይ ከልጅነት ክለቡ ጋር ከተለያየ በኋላ መዳረሻው ወልቂጤ ሆኗል። ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ ብዙዓየው ሰይፉ ነው። የቀድሞ የሮቤ እና ሀላባ ከተማ ተጫዋች አዲስ አበባ ከተማን ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካሳደጉ ተጫዋቾች መካከል እንዱ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም በመዲናው ክለብ አሳልፎ ነበር።

ሦስተኛው ተጫዋች ደግሞ ዳዊት ወርቁ ነው። የቀድሞ የደደቢት እና ወልዋሎ ዓ/ዩ የመሐል ተከላካይ ዓምና የቀድሞ አሠልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌን ተከትሎ መከላከያን ተቀላቅሎ ነበር።