የኢትዮ ኤሌክትሪክ ረዳት አሰልጣኝ ታውቋል

አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ የክፍሌ ቦልተና ረዳት በመሆን በዛሬው ዕለት ተሹመዋል፡፡

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ውድድርን አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቁ በ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ዳግም የሚሳተፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና መሪነት አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾቹን በማቀናጀት በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለትም አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማን ረዳት አሰልጣኝ በማድረግ መሾሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ቡናን በረዳት እንዲሁም ደግሞ በዋና አሰልጣኝነት በመምራት የሚታወቁት አሰልጣኙ በዛሬው ዕለት የክለቡ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው በይፋ የተሾሙ ሲሆን ነገ ክለቡ የዝግጅት ጊዜውን ወደሚያደርግበት አዳማ ከተማ እንደሚያመሩ ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ክለቡ የቀድሞ ተጫዋቹን እና የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ የነበረውን ስምዖን አባይ ፐርፎርማንስ አናሊሲስ በማድረግ መቅጠሩ ተመላክቷል።