የፋሲል ከነማ ተጋጣሚ የሜዳ ላይ ጨዋታውን ከሀገሩ ውጪ ያደርጋል

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ መርሐ-ግብር ከሀገራችን ክለብ ፋሲል ከነማ ጋር የተመደበው የቡሩንዲው ክለብ ቡማሙሩ የሜዳ ላይ ጨዋታውን የት እንደሚያደርግ ታውቋል።

የአህጉሪቱ ሁለት ትላልቅ የክለቦች ውድድር የሆኑት ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ለመሳተፍ እንደየሀገራቱ ኮታ እና ደረጃ ክለቦች የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከጳጉሜ ወር ጀምሮ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በተጠናቀቀው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የፈፀሙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ በመጀመሪያው ዙር የቅድመ ማጣሪያ መርሐ-ግብር በቅደም ተከተል ከሱዳኑ አል-ሂላል ኦምዱርማን እና ከቡሩንዲው ቡማሙሩ ጋር መደልደላቸው ይታወቃል። የሀገራችን ተወካዮችም የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን በባህር ዳር ስታዲየም እንደሚያደርጉ ከሳምንታት በፊት ይፋ መሆኑ ይታወሳል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ ሂላል የሜዳ ላይ ጨዋታውን ካርቱም ላይ ሲያደርግ የፋሲል ተጋጣሚ ቡማሙሩ ግን በሀገሩ (ቡሩንዲ) በካፍ የተፈቀደ ስታዲየም አለመኖሩን ተከትሎ የሜዳ ላይ ጨዋታውን የሚያደርግበትን ስታዲየም ሲፈልግ ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን እንዳረጋገጠችው መረጃ ከሆነ ደግሞ ቡማሙሩ የሜዳ ላይ ጨዋታውን ታንዛኒያ አዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ለማድረግ ወስኗል።