ኤል-ሜሪክ ከሌላ የሀገራች ክለብ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሊያደርግ ነው

በትናትናው ዕለት ከፈረሰኞቹ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደረገው ኤል-ሜሪክ ከሀገራችን ሌላ ክለብ ጋር ተጨማሪ ጨዋታ ሊያደርግ ነው።

የሱዳኑ ክለብ አል-ሜሪክ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የሜዳ ላይ ጨዋታውን በባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም መስከረም 7 የሚያደርግ መሆኑን ተከትሎ ወደ ሀገራችን በመምጣት ቢሸፍቱ ከተማ ላይ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። ከጂቡቲው አርታ ሶላር ጋር ላለበት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታው ይረዳው ዘንድ በትናትናው ዕለት በቢሸፍቱ ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ማድረጉም ይታወሳል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ክለቡ ከሌላኛው የሀገራችን የሊጉ ተሳታፊ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ሁለተኛውን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የአቋም መለኪያ ጨዋታውንም የፊታችን ዓርብ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክሎኖጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም አስር ሰዓት ላይ ለማድረግ መታሰቡን እና የኢንተርናሽናል ዳኞችን ምደባም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን እንዲያስፈፅም ኢትዮ ኤሌትሪክ ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ ማቅረቡን አውቀናል።