አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ጨዋታን ይመራሉ

የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከያዝነው ወር መጨረሻ ጀምሮ የሚከወኑ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ዳኞችም ጅቡቲ ላይ የሚደረግ ጨዋታን እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡

የ2022/23 የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከያዝነው ወር መጨረሻ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት ይከናወናሉ፡፡ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል መስከረም 1 ጅቡቲ ላይ በስታድ ኤል ሀጂ ሀሰን ጉሌድ ስታዲየም የሚደረገውን የአርታ ሶላር እና የኤል-ሜሪክ ጨዋታ አራት ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያዊያን ዳኞች እንዲመሩት መመረጣቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሀል ዳኝነት ሲመራው በረዳትነት ዳኝነት ደግሞ ተመስገን ሳሙኤል እና ፋሲካ የኋላሸት እንደሚሳተፉ ታውቋል። የጨዋታው አራተኛ ዳኛ በመሆን አሸብር ሰቦቃ መመረጣቸውን ሲመላከት ኮሚሽነር ሆነው ደግሞ የሱማሌ ዜግነት ያላቸው ዊሺ ሀጂ ያባሮ ተመድበዋል።

የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ በባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚደረግ የሚታወስ ሲሆን የሱዳኑ ኤል-ሜሪክ ዝግጅቱንም በሀገራችን እያደረገ ይገኛል፡፡