ዋልያዎቹ አዲስ አበባ ገብተው ወደ ሩዋንዳ ያቀናሉ

ወሳኝ ጨዋታቸውን በዚህ ሳምንት መጨረሻ የሚያደርጉት ዋልያዎች በአዲስ አበባ በኩል ወደ ሩዋንዳ እንደሚያቀኑ ታውቋል።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ጨዋታቸውን ወደ ታንዛንያ ተጉዘው ከሩዋንዳን ጋር ያከናወኑት ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያለ ጎል ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። ለመልሱ ጨዋታ ለቀናት ዝግጅቱን በዛው ታንዛኒያ ሲያደርግ የቆየው ብሔራዊ ቡድኑም በዛሬ ዕለት የመጨረሻ ልምምዱን በማጠናቀቅ ከታንዛኒያ እኩለ ሌሊት ላይ በመነሳት አጥቢያ ላይ አዲስ አበባ እንደሚገባ ታውቋል።

በመዲናችን ብዙም ቆይታ የማያደርጉት ዋልያዎቹ በኮኔክሽን ፍላይት ወደ ሩዋንዳ እንደሚያቀኑ ሲታወቅ እግረ መንገዳቸውም ለክለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ የመጡትን ምኞት ደበበ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ሱሌይማን ሀምዲ፣ ጋቶች ፓኖም እና ሄኖክ አዱኛን ዳግም ወደ ቡድኑ በመቀላቀል እንደሚጓዙ ሰምተናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን እሁድ ወሳኙን የመልስ ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን ድል ከቀናው በአልጄሪያ ለሚዘጋጀው የቻን ውድድር ማለፉን የሚያረጋግጥ ይሆናል።