አማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ ግብፅ ሊግ ለማምራት ከጫፍ ደርሷል

ፈጣኑ አጥቂ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ መዳረሺያው ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን ወደ ግብፅ ሊግ ሊጓዝ እንደሆነም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሻምፒዮን የሆነው የመስመር እና የመሐል አጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከክለቡ ጋር ያለው ውል እንደተጠናቀቀና ይታወቃል። ክለቡም ተጫዋቹን ለማቆየት ፍላጎት ሲያሳይ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ከውጪ ክለብ ጋር ግንኙነት በመፍጠሩ ከፈረሰኞቹ የመጣውን ጥያቄ ሳይቀበል ቀርቶ ነበር። ሶከር ኢትዮጽያ ባጣራችው መረጃ መሠረት ተጫዋቹ ወደ ግብፅ ሊግ ለማምራት ከጫፍ እንደደረሰ አውቃለች።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሙሉ ለሙሉ የተለያየው ተጫዋቹ በግብፅ ሊግ ከሚወዳደረው አንድ ክለብ ጋር ድርድሮችን ሲያደርግ ቆይቶ ስምምነት ላይ በመድረሱ የቪዛ እና ተያያዥ ጉዳዮችን እያስጨረሰ እንደሆነ አውቀናል። አማኑኤል የሚያመራበትን የግብፅ ክለብን ለጊዜው ማወቅ ባንችልም ከሰሞኑን ዝውውሩ ይፋ እንደሚሆን ተረድተናል።

ከዳሽን ተስፋ ቡድን ከተገኘ በኋላ ወደ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በማምራት የእግርኳስ ህይወቱን የቀጠለው አማኑኤል አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ጊዜ ድረስ ከሳላዲን ሰዒድ፣ ዑመድ ኡኩሪ፣ ሽመልስ በቀለ እና ጋቶች ፓኖም በመቀጠል አምስተኛው በግብፅ ሊግ የተጫወተ ኢትዮጵያዊ ይሆናል።