አዳማ ከተማ ወሳኙን ተጫዋች ለሳምንታት የማያገኝ ይሆናል

የአዳማ ከተማ የኋላ ደጀን ሚሊዮን ሰለሞን ቀጣይ ጨዋታዎች ያመልጡታል።

ባሳለፍነው ማክሰኞ ክለቡ አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ሚሊዮን ሰለሞን ከእስማኤል ኦሮ አጎዎሮ ጋር በአንድ ለአንድ ትግል ወቅት ከበድ ያለ ጉዳት አጋጥሞት በአስራ አንደኛው ደቂቃ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

ሶከር ኢትዮጵያ የተጫዋቹን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ባደረገችው ማጣራት በግራ እግሩ ላይ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ያጋጠመው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በክለቡ የህክምና ባለሙያ ድጋፍ እየተደረገለት ሲሆን በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የተሻለ ህክምና የሚያደርግ መሆኑን ተነግሮናል። ይህን ተከትሎ የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ እና የአዳማ ከተማ ወሳኝ ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች እንደሚያመልጡት ሰምተናል።