ከፍተኛ ሊግ | አየር ኃይል በቀደመ መጠርያው ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ብቅ ብሏል

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ከአንደኛ ሊጉ አድርጎ በነበረው “መከላከያ ቢ” ምትክ ከዓመታት በፊት ፈርሶ የነበረው አየር ኃይል “ንብ” በሚለው የቀድሞው ስያሜው ሊመለስ ነው።

በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ተወዳዳሪ የነበረው የመከላከያ ቢ ቡድን ወደ ከፍተኛ ሊጉ ካደጉ ክለቦች መካከል አንዱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በአንድ መጠሪያ ስያሜ መወዳደር የሚችለው ክለብ አንድ ብቻ ነው የሚል መመሪያን በማስቀመጡ በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ነገር ተሰምቷል። ይኸውም “መከላከያ ቢ” ለሌላኛው ተቋም የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊት ተላልፎ የተሰጠ በመሆኑ በቀጣይ “ንብ” በሚል መጠሪያ በከፍተኛ ሊጉ ላይ መሳተፍ እንደሚጀምር ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ከአስር ዓመት በኋላ ራሱን ዳግም ወደ እግር ኳሱ ካርታ የመለሰው አየር ኃይል ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ በመሳተፍ ጉዞውን ለመጀመር አዲስ አሰልጣኝም ቀጥሯል፡፡ አዲስ አበባ ከተማን ከከፍተኛ ሊጉ እስከ ፕሪምየር ሊጉ ረዳት አሰልጣኝ እና በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይም ጭምር ክለቡን በጊዜያዊ እና ዋና አሰልጣኝነት ሚና የመምራት ዕድሉን አግኝተው የነበሩት አሰልጣኝ ደምሰው በፍቃዱን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረ ሲሆን ከነገ በስቲያ ቅዳሜ ጀምሮ የ2015 ዝግጅቱን በቢሾፍቱ ከተማ እንደሚጀምር ታውቋል።

“ንብ” በሚል መጠርያ ይበልጥ ዝነኛ የነበረውና በ1953 የኢትዮጵያ ዋንጫን የማንሳት ታሪክ ያለው የቢሾፍቱው ክለብ አየር ኃይል ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልኩ ከጀመረ በኋላ በ1998፣ 1999፣ 2000 እና 2004 ላይ የተሳተፈ ሲሆን 2004 ላይ በያኔው አጠራር ከብሔራዊ ሊግ ባደገበት ዓመት ተመልሶ ወርዶ ከአንድ ዓመት በኋላ በዛው እንደፈረሰ ይታወሳል።

እንደ ንብ ሁሉ ከነባር ክለቦች ቡድኖችን በመረከብ በሊግ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የተለመደ ሲሆን ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢኮሥኮ ቡድኑን ተረክቦ በከፍተኛ ሊግ መሳተፍ መጀመሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።