የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የኦንላይን ቀጥታ ስርጭት ሽፋን ሊያገኝ ነው

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ዛሬ ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች ጋር ባደረገው ውይይት በውድድሩ መጀመሪያ ቀን ፣ በተሳታፊዎች ብዛት እንዲሁም ሊጉ ስለሚያገኘው የቀጥታ ስርጭት ሽፋን አዳዲስ መረጃዎች ይፋ አድርጓል።

የ2015 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በተጠናቀቀው ዓመት ተሳታፊ ያልሆኑ የአማራ ክልል ክለቦችን ጨምሮ በድምሩ 42 ክለቦች በሦስት ምድብ ተከፍለው ይወዳደራሉ፡፡

አስቀድሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ውድድሩ ህዳር 3 እንደሚጀመር አሳውቆ የነበረ ቢሆንም ፌድሬሽኑ ዛሬ ከክለብ አመራሮች ጋር በአፍሮዳይት ሆቴል ካደረገው ምክክር በኋላ የቀን ለውጥ ማድረጉን በድረገፁይፋ አድርጓል። ውድድሩን ቀደም ብሎ በተቀመጠው ቀን እንዲጀመር መወሰኑ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የዝግጅት ጊዜ እንደሚያጥራቸው በመግለፅ እንዲራዘም ከተሳታፊ ክለቦች የተነሳውን ጥያቄ ከግምት በማስገባት ህዳር 10 የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርአት ከተካሄደ በኋላ ውድድሩ ህዳር 17 እንዲጀመር ውሳኔ መሰጠቱን ነው መረጃው የሚያትተው፡፡

በሌላ ዜና ከክለቦች ጋር በተደረገው ውይይት ፌድሬሽኑ ከFIFA ጋር በመነጋገር በፊፋ ፕላስ ፕሮጀክት በኩል ውድድሩ የቀጥታ የኦንላይን ስርጭት እንዲያገኝ ስምምነት የተደረሰ ሲሆን ይህም የውድድሩን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ዓይነተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተገልጿል። በዛሬው የምክክር መድረክ ላይ ከኦንላይን ስርጭቱ ዘላቂ ጥቅም ለማግኘት የውድድሩን ጥራት መጨመር አስፈላጊ መሆኑ መግባባት ላይ የተደረሰበት ሲሆን የከፍተኛ ሊግ ውድድር ኮሚቴ የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር በየዓመቱ በሒደት በመቀነስ ሊጉን ለማስተዳደር አመቺ በሆነ እና ወደ ገበያ ዕድልነት በሚቀይር መልኩ ጥራቱን ከፍ ለማድረግ ከውሳኔ መደረሱን የፌዴሬሽኑ መረጃ ይጠቁማል።

በዚህም መሠረት የ2015 የውድድር ዓመት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር መሳተፍ ያልቻሉ ክለቦችን ጨምሮ 42 ክለቦች በሦስት ምድቦች ተወዳዳሪ የሚሆኑ ሲሆን በየምድቡ 14 ክለቦች ተሳታፊ በማድረግ በዓመቱ መጨረሻ ከየምድቡ የመጨረሻ 5 ደረጃዎች ይዘው የሚያጠናቀቁ በአጠቃላይ 15 ክለቦች ወደ አንደኛ ሊግ እንዲወርዱ ተደርጎ ከአንደኛ ሊግ ደግሞ ለ2016 የውድድር ዘመን 4 ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድጉ ተወስኗል። ይህም በ2016 የሚሳተፉ ክለቦችን ቁጥር በመቀነስ ሦስት የነበረውን ምድብ ወደ ሁለት ዝቅ እንደሚያደርግ ተገልጿል።