ሀዋሳ ከተማ በወንድማገኝ ኃይሉ ዙርያ ያለውን አቋም አሳወቀ

በተጫዋች ወንድማገኝ ኃይሉ ተገቢነት ዙሪያ ሀዋሳ ከተማ ያለውን አቋም ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሳውቋል።

ከዚህ ቀደም ባስነበብናቹሁ ዘገባ በሀዋሳ ከተማ እና በተጫዋች ወንድማገኝ ኃይሉ መካከል ያለመግባባት መፈጠሩን ገልፀን ነበር። ያለመግባባት መነሻውም ሀዋሳ ከተማ ከ2013 እስከ 2016 ጥቅምት 30 ቀን ድረስ ለሦስት ዓመት የሚያቆየው የውል ስምምነት እንዳለው ሲገልፅ ተጫዋቹ በበኩሉ ‘የውል ዘመኔ የሚጠናቀቀው በ2015 ጥቅምት 30 ነው’ በማለት ነበር። ጉዳዩን የያዘው የእግርኳሱ የበላይ አካል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እስካሁን ጥርት ያለ ውሳኔ ሳያሳልፍ ጥቅምት 30 ትናንት አልፏል።

ሀዋሳ ከተማ ተጫዋቹን በውሉ መሠረት ለማቆየት እና ከፍተኛ የደሞዝ ማሻሻያ በማድረግ ለቀናት ለመግባባት ድርድር ሲያደርግ ቢቆይም የወንድማገኝን ይሁንታ ሳያገኝ መቅረቱን አውቀናል። ይህን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ በጉዳዮ ዙርያ ያለውን አቋም ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አሳውቋል።

ክለቡ በደብዳቤው አያይዞ ባቀረበው ሀሳብ መሠረት “በተጫዋቾች የዝውውር መመርያ አንቀፅ 18 ንዑስ አንቀፅ 18 ላይ ማንኛውም ታዳጊ ተጫዋች ለተመዘገበበት ክለብ ለዋናው ቡድን 3 ዓመት የማገልገል ግዴታ አለበት በማለት ያስቀምጣል። ሆኖም በህጉ ላይ የተቀመጠውን ወደ ጎን በመተውም በህገ ወጥ ወኪሎች ተመክሮ ከክለቡ ጋር ቀደም ሲል በገባው ውል ላይ 3 ዓመት ተብሎ የተሞላው እያለ ዓመተ ምህረቱ ላይ 2016 ተብሎ ባለመሞላቱ ብቻ ይህን ተራ ስህተት ነጥሎ በማውጣትና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽኑን ጭምር ለማሳሳት በሞሞከር ተገቢነት የሌለው ክርክር አንስቷል። ይህ የተጫዋቹ ተግባር የአሳዳጊ ክለቡን ያሳዘነ ክለቡ በታዳጊ ተጫዋቾች ያለውን እምነት ጭምር ከማሳጣቱም በላይ ለዚህ ዳኝነት የተቀመጡ ህግ እና ደንብ ጭምር እንዲጣረሱ እያደረገ በመሆኑ ደንቡ እውነተኛና ለማንም የማያዳላ መሆኑ ታውቆ ፌዴሬሽኑ ተጫዋቹ በውሉ መሠረት ክለቡን በታማኝነት እንዲያገለግል ውሳኔ እንዲሰጠን እንጠይቃለን” ብለዋለ።

በዚህ ጉዳይ ላይ በተጫዋቹ በኩል ያለውን አቋም ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ባይሳካም በቀጣይ ምላሹን ለማቅረብ ጥረት የምናደርግ መሆኑን እናሳውቃለን።