መረጃዎች | 26ኛ የጨዋታ ቀን

7ኛ የጨዋታ ሳምንት ነገ ጅማሮውን የሚያደርግ ሲሆን ሁለቱን የነገ መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልቂጤ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ በሆነው መርሃግብር ሰሞነኛ የውጤት መቀዛቀዝ ላይ የሚገኙትን ቅዱስ ጊዮርጊሶችን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከ270 የጨዋታ ደቂቃዎች በኃላ ከድል ከታረቁት ወልቂጤ ከተማዎች ያገናኛል።

ከአስደናቂው አጀማመራቸው ማግስት በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ስድስት ነጥቦች አንዱን ብቻ ያሳኩት ፈረሰኞቹ ከሰሞኑ እያሳዩት የሚገኘው የሜዳ ላይ ብቃት እምብዛም አመርቂ አልሆነም። ምንም እንኳን አሁንም በ13 ነጥቦች በሊጉ አናት የሚገኙት ፈረሰኞቹ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በነገው ጨዋታ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

እንደ ቡድን የነበራቸውን አጠቃላይ ጥንካሬ በሜዳ ላይ ለመድገም እየተቸገሩ የሚገኙት የሚገኙት ፈረሰኞቹ በተለይ የማጥቃት ጨዋታቸው ባለፉት ጨዋታዎች እጅጉን ተዳክሞ ተመልክተናል።በሁለቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች እድሎችን በበቂ ሁኔታ መፍጠር የተሳነው ቡድኑ በሊጉ በስምንት ግቦች ከፍተኛ አስቆጣሪነት ዝርዝሩን እየመራ የሚገኘው እስማኤል ኦሮ-አጎሮም እንዲሁ ከግብ ከራቀ ሁለት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አዲስ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ የሰነበቱት ዳዊት ተፈራ ፣ ተመስገን ዮሐንስ እና ሻይዱ ሙስጠፋ አሁንም በቡድኑ የጉዳት ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።

በሊጉ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ በሊጉ ወደ ድል የተመለሱት ሰራተኞቹ በ9 ነጥቦች በሰንጠረዡ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በጨዋታዎች ቡድኑ አውንታዊ ውጤቶችን ይዞ ለመውጣት አሁንም በጌታነህ ከበደ ላይ ጥገኛ ስለመሆኑ የኤሌክትሪኩ ጨዋታ ዳግም ማረጋገጫ የሰጠ ነበር።

ቡድኑ በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞው ካስቆጠራቸው ሰባት ግቦች አምስቱን ማስቆጠር የቻለው ጌታነህ ከበደ ሲሆን ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች ማግስት በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ያሳዩት ፍላጎት ሆነ የነበራቸው አፈፃፀም በቀጣይ ጨዋታዎች ለቡድኑ ደጋፊዎች ተስፋ የሚፈነጥቅ ሆኗል።

በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ሮበርት ኦዶንካራ ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ እና ኤፍሬም ዘካርያስ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆናቸው ሲረጋገጥ ተመስገን በጅሮንድ እና አፈወርቅ ሀይሉ ግን ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

እስካሁን በሊጉ አራት ጊዜ ሁለቱ ቡድኖች የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአራቱም በማሸነፍ የበላይነት መያዝ ችለዋል።10 ሰዓት ሲል ጅማሮውን የሚያደርገውን ይህን ጨዋታ አዳነ ወርቁ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ መቻል

የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳኩትን ድሬዳዋ ከተማዎችን በሊጉ ከእቅድ በታች ደካማ አጀማመር እያደረጉ ከሚገኙት መቻሎች የሚያገናኘው ጨዋታ ነው።

ወደ ከተማቸው የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዎች ለአምስት ሳምንታት የሚዘልቀውን የከተማቸውን የሊጉ ቆይታ ጠንካራውን ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት አሀዱ ብለዋል። ከተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች በኃላ የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳኩት ድሬዳዋ ከተማዎች በደጋፊያቸው በመታገዝ ይህን አሸናፊነት ለማስቀጠል በዚህኛውም ጨዋታ ከፍተኛ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከተከላካይ ጀርባ በተለይም ቢኒያም ጌታቸውን በማስገባት ኢትዮጵያ ቡና ላይ የበላይነት መውሰድ የቻሉት ድሬዳዎች በዚህኛው ጨዋታም ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ከሚሰጠው መቻል ጋርም ተመሳሳይ ስልት ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ ለነገው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት ከሚያጡት እንየው ካሳሁን ውጭ የተቀረው ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠናል።

በመጨረሻ ጨዋታ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ያስተናገዱት መቻሎች ከ63% በላይ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን መውሰድ ቢችሉም ምንም ዓይነት ዒላማ ሳያደርጉ የመውጣታቸው ጉዳይ የቡድኑን የእስካሁኑን ጉዞ በሚገባ የሚገልፅ ሲሆን አሁንም በተወሰነ መልኩ ጫና ውስጥ የሚገኝ የሚመስለው ቡድኑ በፍጥነት ነጥቦችን በመሰብሰብ ከዚህ ስሜት መላቀቅን አጥብቆ ይሻል።

በመቻል በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት አጥቂው ተሾመ በላቸው እና ተከላካዩ ኢብራሂም ሁሴን ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን የተቀረው ስብስብ ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።

በሊጉ ከዚህ ቀደም አስራ ስምንት ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች መቻሎች በዘጠኝ አጋጣሚ ማሸነፍ ሲችሉ በአንፃሩ ድሬዳዎች ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች እንዲሁም የተቀሩት ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።ምሽት 1 ሰዓት ጅማሮውን የሚያደርገውን ይህን ተጠባቂ ጨዋታ ተከተል ተሾመ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።