ሪፖርት | ሀዋሳ ከ 10 ግንኙነቶች በኋላ ጊዮርጊስን አሸንፏል

በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ኃይቆቹ ከመመራት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች ፈረሰኞቹን 2ለ1 ረተዋል።

በ23ኛው ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ተገናኝተው ፈረሰኞቹ በወላይታ ድቻ 1ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ ቅጣት ላይ በሚገኘው ሞሰስ ኦዶ ምትክ ዳግማዊ አርዓያን ሲያስገቡ ኃይቆቹ በአንጻሩ ሀምበርቾን 1ለዐ ካሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ፀጋአብ ዮሐንስ እና አብዱልባሲጥ ከማል በማይክል ኦቱሉ እና በሲሣይ ጋቾ ተተክተው ገብተዋል።

12፡00 ሲል በዋና ዳኛ ዮናስ ካሳሁን መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተሻለ ንቃት ጨዋታውን መጀመር ችለው 9ኛው ደቂቃ ላይም የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ አማኑኤል ኤርቦ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ የመታው ኳስ ያልተዘጋጀውን ግብ ጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎ ደረት ገጭቶ ተመልሶበታል።

ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የተቸገሩት ሀዋሳዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን ፈጥረው ሰለሞን ወዴሳ በድንቅ ዕይታ የሰነጠቀለትን ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ወደ ውስጥ ለቸርነት አውሽ የቀነሰውን ኳስ ኃይል የለሽነቱ ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ በቀላሉ ይዞበታል።

በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ የቻሉት ፈረሰኞቹ 14ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከግብ ጠባቂው ባሕሩ የተነሳውን ኳስ ዳዊት ተፈራ በረጅሙ አሻግሮለት ከበረከት ሳሙኤል ጋር ሮጦ ያገኘው አማኑኤል ኤርቦ የግብ ጠባቂው የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የመታው ኳስ መረቡ ላይ አርፏል።

ኃይቆቹ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመጠኑ እየተጋጋሉ በመሄድ 19ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ባሻገረው እና በረከት ሳሙኤል በግንባሩ በገጨው ኳስ ጥሩ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ተመልሶባቸዋል። 32ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዓሊ ሱሌይማን ከታፈሰ ሰለሞን በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ በጥሩ ንቃት አግዶበታል።

እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ ፈረሰኞቹ 43ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አማኑኤል ኤርቦ ከበረከት ሳሙኤል እና ሰለሞን ወዴሳ መሃል በመግባት ከመጀመሪያው ጎል በተመሳሳይ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ እንደምንም ብሎ በግሩም ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ማይክል ኦቱሉ እና እስራኤል እሸቱን በአብዱልባሲጥ ከማል እና ቸርነት አውሽ ቀይረው ያስገቡት ሀዋሳዎች ተሻሽለው በመቅረብ ተጭነው መጫወት ሲችሉ 52ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከተሻማ የማዕዘን ምት 54ኛው እና 64ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በዓሊ ሱሌይማን እና እስራኤል እሸቱ አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር።

በሚያገኟቸው ኳሶች ሁሉ ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ መጣራቸውን የቀጠሉት ኃይቆቹ 68ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ሰለሞን ወዴሳ ከረጅም ርቀት በግሩም ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን በፊት ለፊት የመቀስ ምት በመምታት እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ፈረሰኞቹ በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተቀዛቅዘው ሲቀርቡ ይባስ ብሎም ባልተረጋጋው የመከላከል አደረጃጀታቸው ምክንያት ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ሄኖክ አዱኛ በግንባሩ በመግጨት በደንብ ሳያርቀው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው አማኑኤል ጎበና በተረጋጋ አጨራረስ የግብ ጠባቂውን ባሕሩ ነጋሽ እጅ ጥሳ የገባች ጎል ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም ከ10 የእርስ በእርስ ግንኙነቶች በኋላ የተገኘ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንደነበሩ ከዕረፍት መልስ ግን ጥሩ እንዳልነበሩ እና በራሳቸው ስህተት ባስተናገዷቸው ጎሎች እንደተሸነፉ በመጠቆም ሀዋሳዎች በሁለተኛው አጋማሽ ባሳዩት እንቅስቃሴ ድሉ እንደሚገባቸው ገልጸው ከተጫዋቾቻቸው የጠበቁትን እንዳላገኙ ሀሳባቸውን ስጥተዋል።

የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ መሃል ላይ ብልጫ እንደተወሰደባቸው በመናገር በሁለተኛው አጋማሽ ግን በተጫዋች ቅያሪ እንዳስተካከሉት በመናገር በሀዋሳ ቆይታቸው ጊዮርጊስን ለመጀመሪያ ጊዜ ማሸነፋቸው የተለየ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።