ዋልያዎቹ ቀጣይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉባቸው ስታዲየሞች ታውቀዋል

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ቢሳዎ እና ጅቡቲ ጋር ወሳኝ ጨዋታዎች ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለቱን ጨዋታዎች መቼ እንደሚያደርግ እና የት ስታዲየም እንደሚጫወት ሶከር ኢትዮጵያ መረጃ አግኝታለች።

በ2026 በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ዩ ኤስ ኤ አስተናጋጅነት በሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ከጊኒ ቢሳዎ እና ጅቡቲ ጋር የሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠብቁታል። በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኅዳር ወር ከሴራሊዮን እና ቡርኪና ፋሶ ጋር ተጫውቶ ማሸነፍ ያልቻለ ሲሆን ወሳኞቹን ጨዋታዎች ደግሞ ከሜዳው ውጪ የሚያደርግበት ቀን አሁን ታውቋል።

ዋልያዎቹ ግንቦት 29 ከጊኒ ቢሳዎ ጋር እንዲጫወቱ ቀጠሮ ሲያዝ አስገዳጅ ነገር ተፈጥሮ ለውጥ እስካልተደረገ ድረስ ደግሞ ከሦስት ቀናት በኋላ ሰኔ 2 ከጅቡቲ ጋር እንዲፋለሙ ቀን ተቆርጧል። ከጊኒ ቢሳዎ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በብሔራዊ የቢሳዎ ስታዲየም በሆነው ስታዲዮ 24 ሴቴምብሮ ሲደረግ ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በካፍ ፍቃድ ያለው ስታዲየም የሌላት ጅቡቲ ባስመዘገበችው የሞሮኮው ስታድ ኤል አብዲ ኤል ጃዲዳ እንደሚደረግ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።