ሪፖርት | መቻል በምንይሉ ሦስታ ሦስት ነጥብ አግኝቷል

መቻል በምንይሉ ወንድሙ ሦስት ግቦች ጣፍጭ ሦስት ነጥብ በማግኘት ከሊጉ መሪ ንግድ ባንክ ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት ነጥብ አጥብቧል።

በ22ኛ የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አንድ አቻ የተለያዩት መቻሎች አንድ ነጥብ ካገኙበት ፍልሚያ አስቻለው ታመነን በስቴፈን ባዱ እንዲሁም አቤል ነጋሽን በበረከት ደስታ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው በተስተካካይ መርሐ-ግብር በባህር ዳር ከተማ 2ለ1 ከተሸነፉበት ጨዋታ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በለውጦቹም መሳይ ጳውሎስ፣ ዳንኤል ደምሱ፣ ሔኖክ ኢሳይያስ እና ፋሪስ አላዊን በወንድማገኝ ማዕረግ፣ ፉዐድ አብደላ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና መሳይ አያኖ ተክተዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተመጣጠነ እንቅስቃሴ እያስመለከተ ቀጥሎ በ13ኛው ደቂቃ በተሰነዘረ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ የመጀመሪያ ጎል አስተናግዷል። በተጠቀሰው ደቂቃ ወልቂጤዎች ለማጥቃት በወጡበት ሰዓት በፍጥነት ወደ ግብ ያመሩት መቻሎች ከነዓን ማርክነህ ለምንይሉ ወንድሙ አቀብሎት የቡድኑ አምበል ወደ ግብነት በቀየረው ኳስ ግብ ተቆጥሯል።

እንደሁል ጊዜው በማጥቃቱ ረገድ ተዳክመው የታዩት ወልቂጤዎች በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሦስተኛው የማጥቃት ሲሶ እየተገኙ ጥቃቶችን ለማድረግ እምብዛም ያልጣሩ ሲሆን ይባስ በ24ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም የመጀመሪያው ግብ ባለቤት ምንይሉ ከግራ መስመር ዳዊት ማሞ ያሻማውን ኳስ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጓታል።

ጨዋታውን አቅልለው መጫወት የያዙት መቻሎች በ29 እና 30ኛው ደቂቃ በከነዓን ሁለት ጥብቅ ምቶች ለሦስተኛ ግብ ቀርበው ነበር። የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ተጫዋቾች ከወገብ በላይ ሳሳ ቢሉም በ33ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረው ነበር። በዚህም ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘን የቅጣት ምት ተመስገን በጅሮን በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ልኮት ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ደቂቃዎች ሲቀሩት ጨዋታው እጅግ የቀለላቸው መቻሎች እጅግ ሁለት ያለቀላቸው ዕድሎችን ፈጥረው ተመልሰዋል። በ43ኛው ደቂቃ ግን ብልጫቸውን በሁለት ጎል ብቻ ማስቀጠል ያልፈለጉ በሚመስል መልኩ በአምበላቸው ሌላ ድንቅ ጎል ሦስተኛ ግብ አግኝተዋል። አጋማሹም ሦስት ለምንም ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ወልቂጤዎች በተለይ ተጋላጭ የነበረውን የተከላካይ መስመር በሁለት የተከላካይ አማካይ በመሸፈን ሲሰነዘሩ የነበሩትን ጫናዎች አርግበው ለመጫወት ጥረዋል። ቡድኑ ጥቃቱ ረገብ ቢልለትም ወደ ፊት መስመር መሄድ ቀላል አልሆነለትም። ይህ ቢሆንም ግን በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ ሆኖ ታይቷል። በተቃራኒው መቻሎች ከኳስ ጀርባ ዘለግ ያለውን ጊዜ እያጠፉ የወልቂጤ የኳስ ቁጥጥር ፍሬያማ እንዳይሆኑ ማድረግ ተያይዘዋል።

ጨዋታው 67ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወልቂጤዎች የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም መድን ተክሉ ከግራ መስመር ወደ ግብ የመታው ኳስ መረብ ላይ አረፈ ተብሎ ሲጠበቅ አሊዮንዚ ናፊያን በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖታል። ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ግን ወልቂጤዎች ለሁለተኛው አጋማሽ ብርታታቸው ዋጋ ያገኙበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም ጋዲሳ መብራቴ ከቅጣት ምት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ከባዶ ጎል ታድጓል። በቀሪ ደቂቃዎች ወልቂጤዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ይጥራሉ ተብሎ ቢጠበቅም የዳኛው ፊሽካ ሊነፋ ሲል ተመስገን ከሞከረው ሙከራ ውጪ አንድም የሰላ ጥቃት ሳይሰነዝሩ ወተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ የተዳከሙት መቻሎች በበኩላቸው ጨዋታውን ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ በመቆጣጠር ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርባቸው እንዲጠናቀቅ አድርገዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጠ አስተያየት የመቻሉ አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጨዋታው በፈለጉት መልኩ እንደሄደ ጠቅሰው በመጀመሪያው አጋማሽ ተጫዋቾቻቸው ብዙ ስለሮጡና ሦስት ጎል ስላገቡ በሁለተኛው አጋማሽ ረጋ ብለው እንዲጫወቱ እንደፈለጉ ተናግረዋል። አሠልጣኙ ጨምረውም ሦስት ግብ ያስቆጠረው አጥቂያቸው ምንይሉን አድንቀዋል።

የወልቂጤው አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንዳልነበር ገልፀው አጨዋወታቸው በሁለቱ አጋማሾች ሁለት አይነት መልክ እንደነበረውና በሁለተኛው አጋማሽ እንደተጫወቱት መጫወት ቢያስቡም በመጀመሪያው አጋማሽ ካለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እንዲሆን እንዳደረገ አመላክተዋል።