መረጃዎች | 38ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ 10ኛ ሳምንት የሚቋጭባቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን አዘጋጅተናል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ዕኩል ስምንት ጨዋታዎች ያደረጉት ለገጣፎ እና ቡና ለዓመቱ ዘጠነኛ ጨዋታቸው ይገናኛሉ። ለገጣፎ ለገዳዲ ከስድስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ለዚህ ጨዋታ ሲደርስ ሁለት ሽንፈቶች የገጠሙት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመርታት አገግሞ ይቀርባል።

ሊጉን የጀመረበትን አስገራሚ መንገድ ማስቀጠል ያልቻለው ለገጣፎ ለገዳዲ ግብ ማስቆጠር ከተሳነው አምስት ጨዋታዎች አልፈዋል። ቡድኑ ያለበት ሁኔታ በአመዛኙ ከሥነልቦና ጫና ጋር እንደሚያያዝ የመጨረሻው የፋሲል ከነማ ጨዋታ ማስረጃ መሆን ይችላል። ለዚህም ጥሩ በተንቀሳቀሱበት የመጀመሪያ አጋማሽ ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን አግኝተው ሳይጠቀሙ የመቅረታቸው ነገር ማሳያ ነው። ነገም የጨዋታውን መንፈስ መቀየር የሚያስችሉ ቅፅበቶችን የመጠቀም ብቃታቸው በውጤት ደረጃ አንዳች ነገር ይዘው ከመውጣታቸው ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ይመስላል።

ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ከተጋጣሚው በተቃራኒ ተከታታይ ሽንፈቱን የሚረሳበትን ድል በኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ማስመዝገብ መቻሉ አዕምሯዊ ጥንካሬውን ለመመለስ እንደሚረዳው ይገመታል። ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ያሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሦስት ነጥብ ባሳኩበት ጨዋታ ከኋላ በሦስት ተከላካዮች በመጀመር በ3-5-2 አሰላለፍ ጨዋታውን የቀረቡበት ሁኔታ የተስማማቸው ይመስላል። በተለይም ለፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ብሩክ እና መሐመድኑር ይበልጥ ነገሮችን ያቀለለ ሲመስል አጥቂዎቹ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችሏል። አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ነገም ተመሳሳይ አ
ዓይነት አፈፃፀም ከቡድናቸው ሲጠብቁ የኤሌክትሪክን ጨምሮ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ማስተናገዳቸው ግን አሁንም በተከላካይ መስመሩ ላይ ጥያቄ ያስነሳል።

በጨዋታው ለገጣፎ ለገዳዲ ዮናስ በርታ እና አቤል አየለን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አስራት ቱንጆ እና አማኑኤል ዮሐንስን በጉዳት ምክንያት አይጠቀሙም።

10 ሰዓት ሲል የሚጀመረውን ጨዋታ ገመቹ ኤዳሆ ከከፍተኛ ሊጉ በማደግ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ሲሆን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመሰገን ሳሙኤል እና ክንፈ ይልማ ረዳቶች ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

ከሦስተኛው ሳምንት በኋላ ከድል ጋር የተራራቁት ሁለት ቡድኖች ነገ በ10ኛው ሳምንት መጨረሻ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። አርባምንጭ ከተማዎች ላለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈትን ቢያስወግዱም ከአቻ በላይ መራመድ ያልቻሉ ሲሆን አዳማ ከተማ ደግሞ ከተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች በኋላ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል።

በጠንካራ የመከላከል አጨዋወቱ ይታወቅ የነበረው አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻው ጨዋታ ለሁለተኛ ጊዜ ብቻ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። ይህ ለነገ ጨዋታ ይዞ መሄድ የሚገባው መልካም ጎን ቢሆንም በተከታታይ ጨዋታዎች ወደ አሸናፊነት መምጣት መቸገሩ ግን አሳሳቢው ጉዳይ ነው። ቡድኑ ኳስ መቆጣጠርን ከቀጥተኛ አጨዋወት በመቀየጥ ለማጥቃት እየጣረ ቢገኝም የሚፈልገው ስኬት ላይ አልደረሰም። በወላይታ ድቻው ጨዋታም እንዲሁ ለተጋጣሚ መከላከል አመቺ የነበረ ተገማች የማጥቃት አጨዋወቱንም ቀርፎ መምጣት ይጠበቅበታል።

አዳማ ከተማ ጋርም በመከላከሉ ረጋድ ተመሳሳይ ችግር ያለ ሲሆን ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁሉ ግብ ተቆጥሮበት ከሜዳ ወጥቷል። በመጨረሻው የባህር ዳር ጨዋታም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የኋላ መስመሩ ላይ የታየበት ያለመደራጀት ችግር እና የተጋጣሚ አጥቂዎችን ፍጥነት ያለመቆጣጠር ድክመት ለነገም ስጋት የሚሆንበት ይመስላል። በማጥቃቱም በኩል አንደ ዳዋ ሆቴሳ ዓይነት አጥቂዎቹ በግል ከሚያደርጉት ጥረት በተለየ ወጥ የሆነ ደጋግሞ ብልጫ የሚወስድበት የማጥቃት ቅርፅ ይዞ መታየት መቻል ከነገው ጨዋታ በፊት ለቡድኑ የሚያሳስበው ሌላው ነጥብ ነው።

አርባምንጭ ከተማ ከተመስገን ደረሰ ጉዳት ውጪ ቀሪ ስብስቡ ከጉዳት ነፃ ሲሆን አዳማ ከተማ ደግሞ ከሚሊዮን ሰለሞን ውጪ ጉዳት ላይ የነበሩት አብዲሳ ጀማል ፣ አማኑኤል ጎበና እና ጀሚል ያዕቆብ አገግመውለታል።

በሊጉ በ15 ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች አምስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ 11 ግቦች ያስቆጠሩት አርባምንጮች አምስት ጊዜ 10 ግብ ያስቆጠሩት አዳማዎች ደግሞ አራት ጊዜ ድል አድርገዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በዋና ዳኝነት ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድነት ዳኛቸው እና ማንደፍሮ አበበ በረዳትነት እንዲሁም ብርሃኑ መኩሪያ በአራተኛ ዳኝነት ለጨዋታው የተመደቡ አርቢትሮች ናቸው።