የአሠልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 0-2 ባህር ዳር ከተማ

👉 “የዛሬውን ውጤት ለራሳቸው ለተጫዋቾች ነው የማበረክተው” ደግአረገ ይግዛው

👉 “አጋጣሚዎችን ያለ መጠቀማችን ነው እኛን ዋጋ ያስከፈለን” ያሬድ ገመቹ

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው እንደታየው ትልቅ ጨዋታ ነው። ለሁለታችንም ትልቅ ጨዋታ ነው። መሪዎቹ ጋር የሚያቆየንን ድል ነው ያስመዘገብነው። ጨዋታችንን ቀድመን በመጀመሪያው አጋማሽ ማጠናቀቅ የሚል ነበር ይዘን ወደሜዳ የገባነው ፤  ተጫዋቾቹም ያሰብነውን አሳክተዋል። በጥረታቸው ፣ በድካማቸው የሚፈለገውን ነጥብ ይዘው ወጥተዋልና የዛሬውን ውጤት ለራሳቸው ለተጫዋቾች ነው የማበረክተው።

ስለግብ ጠባቂው ፋሲል እንቅስቃሴ…

ፋሲል በተከታታይ ጨዋታዎች ያሳየው ብቃት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው። እንደ ሀገርም ደግሞ በትክክለኛው ሰዓት ላይ ተገኝቷል ብዬ አስባለሁ። ፍጹም ቅጣት ምት ብቻ አይደለም ሌሎች ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አድኗል። ፍጹም ቅጣት ምቱ ግን እንደተባለውም ለእኛ ውጤት ወሳኝ ለውጥ የፈጠረ ሁኔታ ነው። ምክንያቱም እያጠቃን ባለበት የግብ ዕድሎችን እየፈጠርን ባለበት ሁኔታ የተገኘ ስለነበር የተጫዋቾቻችን ሞራል ይጎዳ ነበር። ሆኖም ግን እንደ ቡድን በመጫወታችን ተጫዋቾችም ባደረጉት ጥረት የተሻለ ነገር ይዘን ለመውጣት ችለናል።

አራት ተከታታይ ጨዋታ ስለማሸነፋቸው…

በአጠቃላይ ቡድናችን በእያንዳንዱ ጨዋታ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ፊታችን ላይ ረጅም ጉዞ ነው ያለው እንደሚታወቀው 21 ጨዋታዎች ፊታችን ላይ ይጠብቁናልና ለነዛ ጨዋታዎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን እንጫወታለን። ውጤቱ የሚያደርሰን ቦታ እንደርሳለን።

ስለዋንጫ ማሰብ ስለመጀመራቸው…

እሱን አሁን አናስብም። ስለ ዋንጫ የሚታሰብበት ሰዓት አይደለም ፤ ጉዞው ረጅም ነው። ሆኖም ግን አሁን ባለንበት ቦታ ተረጋግቶ መቆየቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ፊታችን ላይ ትልቅ ጨዋታ ይጠብቀናል። እንግዲህ ለእያንዳንዱ ጨዋታ እንደሚታየው የስብስብ ማነስ አለ በቡድናችን ውስጥ ፤ በጉዳት ተጫዋቾችን እያጣን ነው ያለነውና እንግዲህ ያሉትን ተጫዋቾች እየተጠቀምን ለውድድሩ ሁሌም በአዲስ መንፈስ ሆነን ለመቅረብ ነው የምንሞክረው።


አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው እና ሦስት ነጥብ እንዳያገኙ ስላደረጋቸው ሁነት…

በመጀመሪያው አርባ አምስት ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ያለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ የመጀመሪያው አምስት ደቂቃ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተን ከእዛ በኋላ በርካታ ከእነርሱ በተሻለ ብዙ ኳሶችን ለጎል ቀርበን ሳንጠቀም ቀረን። እነርሱ ያገኙትን ኳስ ተጠቅመው ውጤታማ ሆኑ ፤ እኛን ዋጋ አስከፈለን፡፡

ወደጨዋታው መመለስ ስላልቻሉበት ምክንያት…

የአጨራረስ ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም ነፃ ኳሶች ከአምስት እና ከስድስት በላይ ንፁ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘንባቸው የግብ አጋጣሚ የፈጠርናቸ ነበሩ፡፡ እነዛን ኳሶች አለመጠቀማችን ነው ዋጋ ያስከፈለን እንጂ የእነርሱ ጥንካሬ አይደለም። ያለፍናቸውን ኳሶች ግብ ጠባቂ ነው ያዳናቸው የተወሰኑትን ወደ ውጪ አውጥተናል። ፍፁም ቅጣት ምቱም ተመልሷል። እነዚህ ነገሮች እነርሱን ውጤታማ አድርጓቸዋል፡፡ እነርሱ ደግሞ ያገኙትን ተጠቅመዋል ፣ ሁለተኛው አርባ አምስት እንደውም ወደ እኛ ጎል የሞከሩት ኳስ የለም። አጋጣሚዎችን ያለ መጠቀማችን ነው እኛን ዋጋ ያስከፈለን፡፡

ተደጋጋሚ ውጤት አለማግኘት እና ተፅዕኖው…

ባለፈው ሳምንታት ተጫዋቾች ታመውብን ነበር። ወደ አራት ተጫዋቾች ከቋሚ ተሰላፊዎች ውስጥ አልነበሩም ፤ በእዛ ምክንያት ውጤቶችን አተናል፡፡ ሁለቱ ተመልሰውልናል። በካርድ የወጣ እና አንድ ሁለት ተጫዋቾች ደግሞ በደንብ ስላላገገሙ አልተጠቀምናቸውም፡፡ ስለዚህ ይሄን ያህል ጫና ውስጥ የሚከተን ነገር የለም። ገና ቀሪ ጨዋታዎች አሉን ፤ እነዛ ጨዋታዎች ላይ ጠንክረን ሰርተን ውጤታችንን ማሻሻል እንችላለን፡፡