ሪፖርት | ጦሩ እና ሠራተኞቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ወልቂጤ ከተማ አሁንም በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከመከላከያ ጋር ነጥብ ተጋርቷል።

በ11ኛ የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ገጥመው ሁለት ለምንም የረቱት መቻሎች አጥቂያቸው ምንይሉ ወንድሙን ብቻ በእስራኤል እሸቱ ለውጠው ወደ ሜዳ ሲገቡ በኢትዮጵያ መድን ሁለት ለአንድ የተሸነፉት ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው ሮበርት ኦዶንካራ ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ አፈወርቅ ኃይሉ እና ተመስገን በጅሮንድ በጀማል ጣሰው ፣ ውሀብ አዳምስ ፣ ብዙአየሁ ሰይፈ እና ፋሲል አበባየሁ ምትክ በአሰላለፋቸው አካተው ፍልሚያውን ቀርበዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኳስን ለመቆጣጠር ከፍ ያለ የመሐል ሜዳ ላይ ፍልሚያ የተደረገበት ሲሆን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያስተናገደውም በ12ኛው ደቂቃ ነበር። ወልቂጤ ከተማዎች ጌታነህ ከበደ የመቻልን የመሐል ተከላካይ አሚኑ ነስሩ ተጭኖ በመቀበል በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ወደ ውጪ አውጥቶታል። ወደ ውጪ የወጣው ኳስ የመዓዘን ምት ሆኖ ሲሻማ መቻሎች አምክነውት ወዲያው በፈጣን ሽግግር የግብ ምንጭነት ለማድረግ ጥረው የመጨረሻ የሳጥን ውስጥ ቅብብላቸው ተሳስቶ እጅግ ለግብነት የቀረበው አጋጣሚ መክኗል።

በአንፃራዊነት ወልቂጤ ከተማዎች በራሳቸው አጨዋወትም ሆነ በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ስህተት በተሻለ በተጋጣሚ ሳጥን ሲገኙ የነበረ ሲሆን ግልፅ የግብ ዕድል ግን በቀላሉ መፍጠር አልቻሉም። መቻሎች በበኩላቸው ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት ለመሰንዘር ቢቸገሩም በ40ኛው ደቂቃ ፍፁም ዓለሙ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ በፈጠረው ዕድል እና ከነዓን ማርክነህ ወደ ሳጥን ባሻማው ኳስ መሪ ለመሆን ተንቀሳቅሰው ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እምብዛም የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩበት ያለ ግብ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ መቻሎች በማጥቃቱ በኩል መጠነኛ መሻሻል ያደረጉ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎችም ሁለት ከቆመ ኳስ እንዲሁም አንድ ከክፍት ጨዋታ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ነበር። በተቃራኒው በተጫዋች ለውጥ ከወገብ በላይ ያለው ቅርፃቸው ላይ ሽግሽግ ያደረጉት ወልቂጤዎች በ68ኛው ደቂቃ ብዙዓየሁ ሰይፈ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአጋማሹ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ወደ መቻል ሳጥን አምርተው ግብ አስቆጥረዋል። ሳሙኤል አስፈሪ በረጅሙ የመታውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ከተከላካይ በላይ በመዝለል ጨርፎ ለተመስገን በጅሮንድ ሲያመቻችለት ተመስገን ኳሱን መዳረሻው መረብ አድርጎታል።

መቻሎች ግቡን እንዳስተናገዱ ወዲያው ወደ ጨዋታው ለመመለስ የማጥቃት ኃይላቸው ላይ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ እድሳት ያደረጉ ቢሆንም አሁንም ሮበርት ኦዶንካራን የፈተነ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ፍፁም በግሉ ጥረቶችን ለማድረግ ቢሞክርም በመከላከል ቅርፅ የተሻሉ የነበሩት ወልቂጤዎችን ሰብሮ የሚገባ ዕድል ከእግሮቹ መገኘት አልቻሉም። በ81ኛው ደቂቃ ግን ተስፋዬ አለባቸው ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ በተከላካዮች ተጨርፎ በመከነው አጋጣሚ አቻ ሊሆኑ ነበር። ወልቂጤዎች በበኩላቸው ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ወረድ ብለው እየተጫወቱ የሚያመክኗቸውን ኳሶች በፈጣን ሽግግር እየወሰዱ ለተጨማሪ ግብ ምንጭነት ለመጠቀም ሞክረዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ግን ኳስ በእጅ በመነካቱ መቻል የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ምንይሉ ወንድሙ አስቆጥሮት ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።