ሪፖርት | ወላይታ ድቻ የድሬዳዋ ከተማን የ8 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ ገቷል

የጦና ንቦቹ ብርትካናማዎቹን በማሸነፍ ተከታታይ ድል አስመዝግበው ደረጃቸውን አሻሽለዋል።

በ11ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማን ገጥመው ከከመመራት ተነስተው ሁለት ለአንድ ያሸነፉት ድሬዳዋ ከተማዎች በአሰላለፋቸው ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ የሁለተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታቸውን እንደ ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ በተመሳሳይ ፋሲልን ገጥመው ያሸነፉት ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ሳሙኤል ተስፋዬ እና ሀብታሙ ንጉሴን በመሳይ ኒኮል እና ዘላለም አባቴ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

በቅርብ ሳምንታት በጊዜ የግብ ሙከራዎችን ሲያስተናግዱ የሚታዩት ድሬዳዋ ከተማዎች ይህንን ጨዋታ በፈጣን ጥቃት ነበር የጀመሩት። አንድ ደቂቃ ሳይሞላም ኤሊያስ አህመድ በቀኝ መስመር እየገፋ ሳጥን ውስጥ ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታው ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶበታል። ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በራሳቸው ሜዳ በርከት ብለው በመቆየት ከድሬ ተጫዋቾች የሚያቋርጡትን ኳስ በረጅሙ በመላክ የግብ ምንጭነት ለማድረግ የሞከሩ ሲሆን በዚህ አጨዋወት ግን የጠራ የግብ ዕድል በቀላሉ መፍጠር አልቻሉም።

የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው አድርገው መንቀሳቀስ የቀጠሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ከላይ የገለፅነውን የመጀመሪያ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ጠንካራውን የድቻ የኋላ መስመር መስበር ባይችሉም በተደጋጋሚ ሦስተኛው የሜዳ ክልል እየደረሱ ቀዳሚ የሚሆኑበትን ግብ ፍለጋቸውን ተያይዘዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩም ከቆመ ኳስ እጅግ ለግብ የቀረበ ዕድል ፈጥረው መክኖባቸዋል። በዚህም አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ያሻማውን የቅጣት ምት ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት ተስኗቸው ሱራፌል አግኝቶት ለመጠቀም ጥሮ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል ፤ አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቋል።

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሪያው የተሻለ የሜዳ ላይ ፉክክር የተደረገበት ነበር ፤ የተሻለም የግብ ሙከራዎች ተደርገውበታል። 

በቅድሚያ በመቀመጫ ከተማቸው የሚጫወቱት ድሬዳዋ ከተማዎች ሦስት ተከታታይ ሙከራዎችን አድርገዋል። በዚህም በ51ኛው ደቂቃ ኤልያስ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ የሞከረው ኳስ ሲመለስ ከሳጥኑ ውጪ ቆሞ የነበረው ሔኖክ ሀሰን አግኝቶት አክርሮ መትቶት ለጥቂት ሲወጣበት በ53ኛው ደቂቃ ደግሞ ቢኒያም ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ጋዲሳ ለመጠቀም ጥሮ ከሽፎበታል።

ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ እየሄደላቸው የሚገኘው ወላይታ ድቻዎች በ56ኛው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በግራ መስመር የተገኘ የመዕዘን ምት በበኃይሉ ሲሻማ ቁመታሙ አጥቂ ስንታየሁ መንግሥቱ ከተከላካዮች በላይ በመዝለል መዳረሺያው መረብ አድርጎታል። 

ድሬዎች ከተመሩ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወዲያው መጣር ጀምረዋል። በ63ኛው ደቂቃም ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ቢኒያም በሩቁ ቋሚ በመሆን ለመጠቀም ቢጥርም ሞክሼው የግብ ዘብ ቢኒያም መልሶበታል።

ድሬዎች በቀሪ ደቂቃዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ በማስገባት ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም ነገሮች ቀላል ሊሆኑላቸው አልቻለም። ድቻዎችም በሚደነቅ መታተር ክፍተቶችን እየዘጉ የድሬ የማጥቃት አማራጭ ተሻጋሪ ኳስ ብቻ እንዲሆን ያስገደዱ ሲሆን ተሻሚዎቹንም ኳሶች እያሸነፉ ግባቸውን ሳያስደፍሩ ቀርተዋል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 1-0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።